አይነ-ሥውሩ ሰው
በቄስ ስቲቨን ፓል የተተረከ
አንድ ጊዜ ባልና ሚስት ወደ ሩቅ በረሃ እየተጓዙ ሳለ አንድ አይነ ስውር ሰው መንገድ ላይ ተኝቶ ያገኛሉ፡፡
ባልየውም “ይዘነው እንሂድ፡፡” አለ፡፡
ሚስቱ ግን “አይሆንም ስለማናውቀው ዝም ብለን መንገዳችንን እንቀጥል፡፡” አለችው፡፡
ባልየው ግን አሁንም አሁንም “አይ ይዘነው መሄድ አለብን፡፡” ይላል፡፡ በመጨረሻም ሰውየውን ይዘውት ሄደው ወደ አንድ ከተማ ሲደርሱ አይነ ስውሩም ሰው የሰዎችን ጫጫታና የመኪናዎች ድምፅ ሰምቶ “ይህ መንደር ማን ይባላል?” ብሎ ጠየቀ፡፡
“ይህ ከተማው ነው::” አሉት፡፡
እሱም “ከተማ ነው? እሺ እንሂድ” አለ፡፡
ከተማው ዘንድ እንደደረሱም ዓይነ ስውሩ ሰው መጮህና ማልቀስ ጀመረ፡፡ ሰዎችም ሮጠው ወደርሱ መጥተው “ምን ሆነሃል?” አሉት፡፡
እርሱም “ይህ ሰው ዓይነ ስውርነቴን አይቶ ሚስቴን ቀማኝ፡፡” አላቸው፡፡
ሰዎቹም የተናገረውን በማመን “እውነት ነው፡፡” አሉት፡፡
ባልየውም “አይደለም እሷ የዓይነ ስውሩ ሚስት ሳትሆን የእኔ ሚስት ናት፡፡” አለ፡፡
ከዚያም ፍርድ ለማግኘት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄዱ፡፡ ከጣቢያውም እንደደረሱ መርማሪው ፖሊስ ሶስቱንም በተለያዩ ክፍሎች አስገባቸው፡፡
በመሸ ጊዜም ሰዎቹ መጥተው ተደብቀው እያንዳንዱን ክፍል ያዳምጡ ጀመር፡፡
ዓይነ ሥውሩም “መጮህና ማልቀሴ እኮ ብልጠቴ በጀኝ፡፡ ይህንን ሁሉ ባልዋሽ ኖሮ ምንም አላገኝም ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ውሸት መሆኑን አያውቁም፡፡” እያለ ሲያወራ ሰሙት፡፡
ከዚያም ወደ ሴትየዋ ክፍል ሄደው እሷም “ለባሌ እንደዚህ አይነት ነገር ያጋጥመናል ብዬው ነበር፡፡ ነገር ግን እኔ ያልኩትን ነገር አልሰማ ብሎ ዓይነ ስውሩን አስከትለን እንድንመጣ ወተወተኝ፡፡ አሁን ታዲያ ይኸው ችግር ውስጥ ገባን፡፡” ስትል ሰሟት፡፡
ቀጥሎ ከባልየው ክፍል ሄደው ማዳመጥ ጀመሩ፡፡
እሱም “ይህ የእኔ ስህተት ነው፡፡ የሚስቴን ምክር አልሰማ ብዬ፤ ይህ ሁሉ የእኔ ስህተት ነው፡፡” ሲል ሰሙት፡፡
በዚህ ሁኔታ ሶስቱንም በአንድ ጠርተው አይነ ስውሩን ሰው ወንጅለው ካሰሩት በኋላ ባልና ሚስቱን ለቀቋቸው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|