ጋንያና ጅቡ
በኒያል ጋትች የተተረከ
ጋንያና ልጁ ለአደን ወደ ጫካው ቢሄዱም ምንም የሚያድኑት ስላጡ በጣም ራባቸው፡፡ ከጠዋት እስከ ማታ ቢያድኑ ቢያድኑ ምንም አጥተው በመጨረሻ አንድ ጅብ ገደሉ፡፡ ሆኖም ኑዌሮች ጅብ አይበሉም፡፡
እርስ በእርስም “ምን እናድርግ? ጅቡን ካልበላን እንሞታለን ከበላነው ደግሞ ባህላችንን እናጎድፋለን፡፡” ተባባሉ፡፡
ትንሽ ካሰቡም በኋላ ጋንያ “አዎ! መልሱን አግኝቸዋለሁ፡፡ መጀመሪያ የጅቡን ጭንቅላት ቆርጠን እንጣለው፡፡” አለ፡፡
እንደዚያም አደረጉ፡፡
ከዚያም ጅቡን እያየ እንደገና አሰበና “አሁን ደግሞ እግሮቹን ቆርጠን እንጣል፡፡” አለ፡፡
እግሮቹንም ቆርጠው ጣሉ፡፡
“አሁን ደግሞ ጭራውን እንቁረጥ፡፡” አለ ጋንያ፡፡ ጭራውንም ቆርጠው ጣሉ፡፡
ከዚያም ጋንያ “እንግዲህ አሁን ድኩላ ስለሆነ ቆዳውን እንግፈፈውና አብስለን እንብላው፡፡” አለ፡፡ ታሪኩም ይኸው ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|