ኩላንግ በእስር ቤት
በኒያል ጋትች የተተረከ
አንድ ከጋምቤላ አቅራቢያ የሚኖርና ብዙ ምግብ መብላት የሚወድ ሰው ነበር፡፡ ብዙ ምግብ የምታዘጋጅለት ጥሩ ሚስት ነበረችው፡፡ ለቁርስ ብዙ ምግብ፣ ለምሳ ብዙ ምግብ፣ ለእራት ብዙ ምግብ ታዘጋጅለት ነበር፡፡
ነገር ግን ከጊዜ በኋላ ችግር ስለነበረበት ወደ ጋምቤላ እስር ቤት ወረደ፡፡
ታዲያ እስር ቤት ሲገባ የነበረው ምግብ በጣም ትንሽ ስለነበረ ይርበኛል ብሎ ፈራ፡፡ ስለዚህ ትንሽ ምግብ በልቶ ጨጓራውን ከሚቀሰቅስ አለመብላትን መረጠ፡፡ አንድ ቀን አለፈ፤ ምንም ምግብ አልበላም፤ በሁለተኛውም ቀን ምንም ምግብ አልበላም፤ ሶስተኛውም ቀን ያለ ምግብ አለፈ፡፡
ነገር ግን የወህኒ ቤቱ ሃላፊ በጉዳዩ በጣም ስለተጨነቀ ሰዎቹን ጠርቶ “ይህ ሰው ካልበላ ስለሚሞት ጥሩ አይደለም፡፡” አላቸው፡፡
እነርሱም “አዎን ነገር ግን እዚህ ያለው ምግብ ጥሩ አይደለም፡፡ ሚስቱ በጣም ጥሩ ምግብ ታዘጋጅለት ነበር፡፡” አሉት፡፡
እርሱም “እንግዲያው ሚስቱን እጠራታለሁ፡፡ የት ነው ያለችው?” ብሎ ጠየቀ፡፡
እነርሱም እሷ ያለችው ሌላ ከተማ ውስጥ እንደሆነ ነገሩት፡፡ ስለዚህ ስልክ ፈልጎ የሰውየው ሚስት ጋ በመደወል “ባልሽ ምግብ እየበላ ስላልሆነ የቻልሽውን ያህል ምግብ ሠርተሽ ይዘሽ ወደኛ ነይ፡፡” አላት፡፡
እሷም ስልኩን በአስቸኳይ ዘግታ ያለውን ምግብ ሁሉ ሰብስባ ካዘጋጀች በኋላ ወደ እስር ቤቱ ይዛ ሄደች፡፡
ሰውየውም በጣም ተርቦ ስለነበር የመጣውን ምግብ ሁሉ ከበላ በኋላ የወህኒ ቤቱን ሃላፊ ጠርቶ “ከታሰርኩ ገና ሶስት ቀኔ ነው፡፡ የምኖርበት መንደር ደግሞ ከእዚህ በጣም ብዙ ይርቃል፡፡ እናም ሚስቴ እንዴት አንደዚህ ፈጥና ልትደርስ ቻለች?” ብሎ ጠየቀው፡፡
የወህኒ ቤቱም ሃላፊ “ስልክ ደውዬላት ነው፡፡” አለው፡፡
ሰውየው ግን ስልክ ምን እንደሆነ ስለማያውቅ ስልክ ማለት ወደ መንደሩ ሮጣ በመሄድና ሚስቱን ይዛ መጥታ ምግቡን የሰራችው አንዲት ወጣት ሴት ልጅ ናት ብሎ አሰበ፡፡
እናም “እባካችሁ ቴሌፎንን አሳዩኝ፡፡ እንደዚህ ፈጣን ከሆነች እኔም ላገባት እፈልጋለሁ፡፡” አለ ይባላል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|