ዝሆንና አውራ ዶሮ
በኒያል ጋትች የተተረከ
አንድ ዝሆንና አንድ አውራ ዶሮ ነበሩ፡፡ ዝሆኑም ሁልጊዜ በትልቅነቱና በጥንካሬው በመኩራራት ተወዳጅ ለመሆን ይሞክር ነበር፡፡ ሆኖም ምንም እንኳን አውራ ዶሮው በመጠን ትንሽ ቢሆንም በጣም ብልጥ ነበር፡፡
ታዲያ አንድ ቀን ዝሆኑን “አንተ ትልቅ ብትሆንም ምንም ማለት አይደለም፡፡ አንጎል አንጂ መጠን ምንም አያደርግም፡፡” አለው፡፡
ዝሆኑ ግን “አይደለም አንተ ደደብና ትንሽ እንስሳ ነህ፡፡ ከእኔ ጋር ልትወዳደርም ሆነ ልትስተካከል አትችልም፡፡” አለው፡፡
ዶሮውም “እንግዲያው እንወዳደርና ብዙ ውሃ ማን መጠጣት እንደሚችል እንመልከት፡፡” አለው፡፡
ስለዚህ ወደ አንድ ትልቅ ወንዝ ምናልባትም ወደ ባሮ ወይም አኮቦ በመሄድ ሌሎች እንስሳት ሁሉ አንዲፈርዱ ጠየቋቸው፡፡
ውድድሩም ሲጀመር ዶሮው ምንቃሩን ዝሆኑም ኩምቢውን ውሃው ውስጥ ከተው መጠጣት ጀመሩ፡፡
ሆኖም ዶሮው ግን እየጠጣ አልነበረም፡፡ ምንቃሩን ብቻ ውሃው ውስጥ አድርጎ እየከፈተ ይዘጋው ነበር፡፡ ዝሆኑ ግን ውሃውን ጠጥቶ ጠጥቶ ሆዱ አበጠ፡፡
በመጨረሻም በጠጣው ውሃ ብዛት ፈንድቶ ሞተ፡፡
ይህ የሚያሳየው መጠን ሳይሆን ብልጠት መሻሉን ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|