ጅብና ቀበሮ
በፓስተር ጄምስ ዱዎትዶል የተተረከ
አንድ ቀን አንድን ጀብ እናቱ የማገዶ አንጨት ከጫካ ይለቅም ዘንድ ትልከዋለች፡፡ ሆኖም ጅቡ ርቦት ነበር፡፡ በመንገዱም ላይ አንድ ቀበሮ አገኘ፡፡ ጅቡ የቀበሮው አጎት ስለነበር ተዋወቁ፡፡
አጎቱ መራቡን አይቶ ቀበሮው “ለምን ወደቤት አብረን ሄደን እህቶችህ ምግብ አይሰጡህም? እዚህ ጫካ ውስጥ እየተራብክ እኮ ነው፡፡” አለው፡፡
ጅቡም “እውነትም ርቦኛል፡፡ ለሁለት ቀናት አልበላሁም፡፡ ነገር ግን አብሬህ አልሄድም፡፡” አለው፡፡
“ለምንድነው አብረኸኝ የማትሄደው?” አለው ቀበሮው፡፡
ጅቡም “ካንተ ጋር አብሬህ የማልሄደው ጠላቶቼ ሊገድሉኝ ስለሚችሉ ፈርቼ ነው፡፡” ብሎ መለሰለት፡፡
ቀበሮውም አጎቱን እንዲህ በማለት ገፋፋው “ጠላቶችህን ከፈራህ ከማገዶ ጋር አብሬ አስሬህ ልደብቅህና ከቤትህ ስትደርስ እህቶችህ ደብቀውህ ትኩስ ምግብ ይሰጡሃል፡፡”
በዚህም ተስማምቶ ከማገዶው ውስጥ አብሮ ታሠረ፡፡
ቀበሮው ከቤቱ ደጃፍ ሲደርስ ማገዶውን ከቤቱ አጠገብ አስቀመጠ፡፡ ነገር ግን ለእናቱ ምንም አልነገራትም፡፡ እናቱም ምግቡን በምታማስልበት ማንኪያ ለቀበሮው ምግብ ስትሰጠው ቀበሮው በድብቅ ወጥቶ ምግቡን ለተራበው ጅብ ሲሰጠው ጅቡ ማንኪያውን ከምግቡ ጋር አብሮ ዋጠው፡፡ እናትየውም የተጣደው ምግብ እያረረባት ስለሆነ ቀበሮው ማንኪያውን እንዲያመጣላት ወተወተችው፡፡
ቀበሮውም ወደ ጅቡ ሮጦ በመሄድ ጅቡ ማንኪያውን እንዲያስታውክ ጠየቀው፡፡
ጅቡም “የእህቴ ልጅ ሆይ ማንኪያውን ስለዋጥኩት ይቅርታ አድርግልኝ፡፡ በጣም ርቦኝም ስለነበረ ማንኪያው ጨጓራዬ ውስጥ ገብቷል፡፡” አለው፡፡
ቀበሮውም እያለቀሰ ወደ እናቱ ሮጦ በመሄድ ትንሽ እንድትታገሰው ጠየቃት፡፡ እናቱንም ትልቅ ዱላ እንድትሰጠውና የታሰረው ማገዶ ውስጥ ብዙ ጊንጦች ስላሉ ልደብድባቸው ብሎ ጠየቃት፡፡ እናቱም ዱላውን ሰጥታው ወደ ማገዶው ሄዶ ማገዶውን ባለ በሌለ ሃይሉ በመምታት ከውስጥ ያለውን ጅብ አገኘው፡፡
ከዚያም ጅቡ ዱላው ስለጠናበት ጮክ ብሎ እየጮኸ ወደ ጫካው ሮጦ ሄደ፡፡ እናትየውም ቀበሮው ለምን እንደዚያ እንዳደረገ ስትጠይቀው ቀበሮው “ያንን ያደረኩት አጎቴ ማንኪያውን ስለዋጠው ነው፡፡” አላት፡፡
በዚህ ምክንያት ነው ጅብ እስካሁን አንካሳ ሆኖ የቀረው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|