የዱር አይጥና አንዲት ሴት
በሳምቦ ሊካሳ ሃያ የተተረከ
በአንድ ወቅት አንድ የዱር አይጥ አንዲት እጅግ በጣም ቆንጆ ሴት አይቶ ይወዳትና እንዴት እንደሚቀርባት ግራ ገባው፡፡ እናም አንድ ቀን በጣም ዝናባማ ቀን ከደጇ ተቀመጠ፡፡
ሆኖም በጣም ስለበረደውና ዝናቡ ስላረጠበው እየተንቀጠቀጠ “እባክሽ አንቺ ደግ ሴት እዚህ በጣም ብርድ ስለሆነ በጣሪያው ክፈፍ ስር አድርጌ ወደ ውስጥ ልግባ?” ብሎ ጠየቃት፡፡
እሷም “አዎ ግባ” አለችው፡፡
እናም ወደ ውስጥ ገብቶ ከበሩ አጠገብ ተቀመጠ፡፡ በብርዱ መንቀጥቀጡን ቀጥሎ እንዲህ አላት “እባክሽ አንቺ ሴት ሆይ ወደ እሳቱ ተጠግቼ ብቀመጥ ይሞቀኛል፡፡”
እሷም “አዎ እባክህ ናና ወደ እሳቱ ተጠግተህ ቁጭ በል” አለችው፡፡
ስለዚህ ወደ እሳቱ ተጠጋ፡፡
ከቆይታ በኋላ እርጥበቱ ቢደርቅለትም አሁንም የበረደው በመምሰል “እባክሽ ውዷ ሴት አሁንም እየበረደኝ ነው፡፡ ከምንጣፍሽ አጠገብ መጥቼ ልተኛ?” አላት፡፡
እናም ከቁርበቱ አጠገብ ተኛ፡፡
ከዚያም “አሁንም በርዶኛል ቁርበቱ ላይ ልተኛ?” አላት፡፡
እሷም “እሺ ቁርበቱ ላይ መተኛት ትችላለህ፡፡” አለችው፡፡ ቁርበቱም ላይ ወጥቶ ከተኛ በኋላ ትንሽ ቆይቶ “እንቅልፌ እየመጣብኝ ነው፡፡ ክንዶችሽ ላይ ብተኛ ቅር ይልሻል?” አላት፡፡
“አዎ ትችላለህ፡፡” አለችው፡፡
ከዚያም ሁለቱ ተጋብተው በደስታ አብረው መኖር ጀመሩ፡፡
የዚህ ታሪክ መልዕክትም ፍላጎቱ ካለ ዘዴ አይጠፋም የሚል ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|