አንካሳው ሰው
በሳምቦ ሊካሣ ሃያ የተተረከ
ሚስትና ሶስት ሴት ልጆች የነበሩት ሰው ነበር፡፡ በደስታም አብረው እየኖሩ ሳለ ባልየው ሞተ፡፡ ከጊዜ በኋላም ሚስትየው ሌላ ሰው ማግባት ብትፈልግም ልጆቿ ሌላ አባት እንደማይፈልጉ ታውቅ ነበር፡፡ ሆኖም ሺጎሽ ከሚባል ሰው ጋር መውጣት ጀመረች፡፡
ሺጎሽም የእናትየው አዲስ ፍቅረኛ ሆነ፡፡ እሷ ግን ልጆቹ እንዲያውቁ አልፈለገችም፡፡
ስለዚህ ወደ አንድ ግዙፍ ዛፍ አጠገብ ሄዳ እየተጣራች በቆንጆ ድምጿ እንዲህ እያለች ትዘፍን ነበር፡፡
“ሺጎሽ፣ሺጎሽ
እዚህ ናና አግኘኝ
እዚህ ትልቁ ዛፍ ስር አግኘኝ”
ሺጎሽም ከጓደኞቹ ወይም ከሌሎች ሰዎች ጋር ስለሚሆን እርሱም እየዘፈነ ይመጣና እንዲህ ብሎ ያለቅሳል፡፡
“ሚስቴ መጣችልኝ
ሚስቴ መጣችልኝ”
ሺጎሽ አንድ ታፋው ሰባራ ስለነበረ ዘፈኑም የሚከተለውን ቅላፄ ነበረው፡፡
“አዎ መጣሁልሽ
“አዎ መጣሁልሽ
እናም ማንከሱ በዘፈኑ ውስጥ ይታወቅ ነበር፡፡ በዚህ ዓይነት ወደ ዛፉ ስር እየሄደ አውርተውና ፍቅራቸውን ጨርሰው ይለያዩ ነበር፡፡
እርሷ ወደ ልጆቿ ስትመለስ እሱም ወደ ጓደኞቹ ተመልሶ ይሄዳል፡፡ ታዲያ ልጆቹ ጉዳዩን ባወቁ ጊዜ አባታቸው በሌላ ሰው እንዲተካ ስለማይፈልጉ በጣም ተበሳጩ፡፡ ስለዚህ ሺጎሽን ለመበቀል ወሰኑ፡፡
ወደ አንድ ሙልጭልጭ ቅርፊት ወዳለው ዛፍ ሄደው ቅርፊቱን ልጠው በማምጣትና ውሃ ውስጥ በመዘፍዘፍ ይበልጥ እንዲያዳልጥ አደረጉት፡፡ ከዚያም ሺጎሽ በሚመጣበት መንገድ ላይ አኖሩት፡፡
የመጨረሻዋም ልጅ የእናቷን አይነት ድምፅ ስለነበራት ሶስቱም ዛፍ ላይ ወጥተው ትንሿ ልጅ እንዲህ እያለች መዝፈን ጀመረች፡፡
“ሺጎሽ፣ሺጎሽ
ናልኝ ዛፍ፣ ስር ነኝ”
ሺጎሽም የፍቅረኛው ድምፅ መስሎት “ሚስቴ መጣችልኝ፤ ሚስቴ መጣችልኝ” የሚለውን ዘፈኑን እየዘፈነ በአንካሳ እግሩ በመንገዱ እየተቻኮለ ሄደ፡፡
የሚያዳልጠው የዛፍ ቅርፊት ላይም ስለቆመና ክፉኛ ወድቆ በአንካሣ እግሩ ላይ ሌላ ጉዳት ስለደረሰበት እዚያው ወድቆ ሳለ ልጆቹ ከዛፉ ላይ ወርደው በዱላ ቀጥቅጠው ገደሉት፡፡
ከዚያም ከእናታቸው በመሸሽ ወንዙን ተሻግረው ከአንድ ትልቅ ዛፍ ላይ ተደበቁ፡፡
ዛፉ ላይ እንደተደበቁም “እማማ፣ እማማ ፍቅረኛሽ እየጠበቀሽ ነው፡፡” እያሉ ከዛፉ ላይ ተጣሩ፡፡
እናታቸውም ልጆቹ ስለፍቅረኛዋ እንደማያውቁ ስለምታስብ በጣም ደነገጠች፡፡ ለማንኛውም ወደ ትልቁ ዛፍ እየሮጠች ሄዳ ዙሪያውን ስትመለከት ማንም ሰው አልነበረም፡፡ የዝንቦቹ ድምፅ ብቻ ስለነበረ ከቁጥቋጦው ስር ስትመለከት የፍቅረኛዋን አስከሬን አየች፡፡
እጅግ በጣም ተናዳ ከወንዙ አሻግራ ስትመለከት ልጆቿን ከትልቁ ዛፍ ላይ አየቻቸው፡፡ ወንዙን አቋርጣ ዛፉን ቀና ብላ ስትመለከት ሶስቱንም ልጆቿን ቅርንጫፎቹ ላይ አየቻቸው፡፡
ከዚያም የመጀመሪያዋን “የበኩር ልጄ ሆይ አንቺ ልጄ ስለሆንሽና ከማህፀኔ የወጣሽ በመሆኑ እንደማልጎዳሽ ታውቂያለሽ፡፡ ነይ ውረጅ::” አለቻት፡፡
የመጀመሪያ ልጇም “አልወርድም::” አለቻት፡፡
እንደገና ቀና ብላ አይታ “ሁለተኛዋ ልጄ ሆይ! አንቺ ልጄ ነሽ፤ ስጋና ደሜ ነሽ፡፡ የምጎዳሽ ይመስልሻል? ነይ ውረጅ፡፡” አለቻት፡፡
ሁለተኛዋም ልጅ “እምቢ” አለች፡፡
ከዚያም ወደ ትንሿ ልጅ ተመልክታ “አንቺ ትንሿ ልጄ ስለሆንሽ በጣም እወድሻለሁና ነይ ውረጅ፡፡” አለቻት፡፡
ልጅቷም እምቢ አለች፡፡
ስለዚህ እናትየው በጣም ተበሳጭታ መጥረቢያ በማምጣት ዛፉን መቁረጥ ጀመረች፡፡ በመጨረሻም ዛፉ ከወንዙ ላይ ወደቀ፡፡
ዛፉም ወንዙ ላይ በወደቀ ጊዜ እንደ ድልድይ ስለሆነ የመጀመሪዋና ሁለተኛዋ ልጆች ሮጠው ሲያመልጡ ሶስተኛዋ ልጅ ግን አንድ ትልቅ ቅርንጫፍ ታፋዋ ላይ ስለወደቀባት አጥንቷ ተሰበረ፡፡ ስለዚህ ቀሪውን ህይወቷን አንካሳ ሆና ቀረች፡፡
የዚህ ተረት መልዕክትም በሌሎች ለመሳቅም ሆነ ሌሎችን ለመጉዳት አትሞክር፡፡ አንድ ቀን አንተም እንደነሱ ልትሆን ትችላለህና የሚል ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|