የመሬት ባላባቱ
በዱዋል ፑል የተተረከ
በአንድ ወቅት አንድ አስቸጋሪ የመሬት ባላባት ነበር፡፡ አህያና ግዙፍ መሬትም ነበረው፡፡ ግዛቱ ላይ በአህያው እየጋለበና በጠባቂዎቹ ታጅቦ እየተዘዋወረ ጭሰኞቹን ያስቸግር ነበር፡፡
እንደዚህም ይላቸው ነበር “ጠንክራችሁ ሥሩ ካለበለዚያ እቀጣችኋለሁ:: በደንብ አምርቱ፡፡”
እንደዚህ ጠንካራ ትዕዛዞችን ሁልጊዜ እያስተላለፈ ጭሰኞቹን በጣም ያሰቃያቸው ነበር፡፡
በዚያን ጊዜ የመሬት ባላባቶች ማን ጥሩ እርሻና ማን ጥሩ ምርት አለው በማለት እርስ በርስ ይፎካከሩ ነበር፡፡ ታዲያ ይህ የመሬት ባላባት ውድድሩን በተሸነፈ ጊዜ የተወሰኑትን ጭሰኞች ይገድል ነበር፡፡ ከእለታት አንድ ቀን ታዲያ አንድ ጎበዝ የነበረ ጭሰኛ የባላባቱ አመል በጣም ስላበሳጨውና ስለሰለቸው ወደ ባላባቱ ቤት ሄዶ “የእኔ ምርት ደርሷልና የገብስ ጠላ ስለጠመኩ ወደእኔ እቤት መጥተው እባክዎ ጠላ ይጠጡ፡፡” አለው፡፡
ወደጭሰኛውም ቤት እየሄዱ ሳለ ባላባቱ አህያውን ሲጋልብ ጭሰኛው ከጎኑ ከጎኑ ይሄድ ነበር፡፡ ነገር ግን ጭሰኛው መንገዱ ላይ ገመድ አስሮ ስለነበረ ባላባቱ ሳያይ አህያው ተደናቅፎ ወደቀ፡፡
ባላባቱ በወደቀም ጊዜ ተጎድቶ ነበርና ጭሰኛው “ይሄ ደደብ አህያ አውቆ ነው የተደናቀፈው፡፡ አህያውን ያባሩትና በእግራችን እንሂድ፡፡” አለ፡፡
አህያውንም አባረው መንገዳቸውን በእግር ቀጠሉ፡፡ ረጅምና የዱር ሰጎን በምትገኝበት ጫካ በኩል ሲሄዱ ሰጎኗ የመንደሩን ሰዎች የምታውቅ ሲሆን እንግዳ ሰዎችን ግን ታጠቃ ነበር፡፡
እናም ሰጎኗ ባላባቱን እየጠቀጠቀች ስለጎዳችው ለማምለጥ ሲል ሮጠ፡፡ ነገር ግን ሰጎኖች በጣም ፈጣን እንስሳት ስለሆኑ ሰጎኗ እያባረረች ስለረጋገጠችው የመሬት ባላባት ከመሬት ወድቆ ሞተ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|