የሎተሪ ቲኬቱ
በዱዋል ፑል የተተረከ
ከረጅም ጊዜ በፊት በጣም ደሃ የነበሩ ሁለት ጓደኛሞች ነበሩ፡፡ ብዙ ችግሮችንም በጋራ በመጋፈጥ አብረው አደጉ፡፡ በርግጥ አብዛኛውን ጊዜአቸውን የሚያጠፉት እንጨት በመልቀም ነበር፡፡ ትንሽ ገንዘብ ሲያገኙ ለምግባቸው ብቻ ስለሚያውሉት ህይወት ለእነርሱ በጣም ከባድ ነበረች፡፡
ታዲያ አንድ ቀን አንደኛው “እንደዚህ አይነት ተስፋ ቢስ ኑሮን እስከ መቼ ነው የምንገፋው? ለአንድ ወይም ለሁለት ቀናት ተርበን ሎተሪ እንግዛ፡፡ ትልቁን እጣ እናሸንፍ ይሆናል፡፡” አለ፡፡
ጓደኛውም “አይሆንም እኔ መራብ አልፈልግም፡፡ ድርሻዬን እበላለሁ፡፡” አለ፡፡
እናም አንደኛው ጓደኛ ተርቦ ቲኬት ገዛ፡፡ ምግቡን የወሰደው ጓደኛ ግን “ቲኬቱን እኔ ልቁረጥልህ” ብሎ ቆረጠለት፡፡
ዕጣው የሚወጣበት ቀን ሲደርስ ያቺ ቲኬት የትልቁ ሽልማት አሸናፊ ሆነች፡፡
ቲኬቱን የገዛው ጓደኛም እጣው ስለወጣለት በጣም በመደሰት ወደ ጓደኛው እየሮጠ ሲሄድ ጓደኛው ገንዘቡን ተቀብሎ ስለነበር “ማንነትህን እንኳን አላውቀውም፡፡ የማላውቅህ ሰው ነህ፡፡” ብሎ አባረረው፡፡
ከዚያ በገንዘቡ ትልቅ ቪላ ቤትና መኪና ገዝቶ ሚስት አገባ፡፡ ሌላኛው ጓደኛ ግን ወደ ድሮው ህይወቱ ተመልሶ እንጨት በመልቀም ወደ ገበያ ወስዶ መሸጡን ቀጠለ፡፡
አንድ ቀን ታዲያ የሃብታሙ ሰው ሚስት ድሃውን ጓደኛ ገበያ ቦታ አየችው፡፡ የባሏ ጓደኛም እንደነበረ ስለምታውቅ እቃዋን ተሸክሞ ቤት እንዲያደርስላት ሰጠችው፡፡ ከቤት ሲደርሱም ወደ ቤት አስገብታ ምግብ ሰጠችው፡፡ ከዚያን ዕለት ጀምሮ ሁልጊዜ እቃዋን ከገበያ ተሸክሞ እንዲያደርስላት በማድረግ ምግብ ትሰጠው ጀመር፡፡ ስለየራሳቸው ማውራትም ጀመሩ፡፡ እርሱም ስላለፈው ሁሉ እያነሳ ባሏ እንዴት እንደካደው ነገራት፡፡
ሚስትየውም በጣም ስለተበሳጨች ሳጥኑ ውስጥ ያለውን ገንዘብ በሙሉ አውጥታ ከሰጠችው በኋላ “ይህ ያንተ ገንዘብ ነው፡፡” አለችው፡፡ ባሏም ተመልሶ በመጣ ጊዜ ገንዘቡን ከቦታው ስላጣው በጣም ተናደደ፡፡ ሚስቱም “ምናልባት ሌባ መጥቶ ሰርቆት ይሆናል::” አለችው፡፡ ሆኖም በጣም ተበሳጭቶ ስለነበረ ሚስቱን ከቤት አባሮ ቤቱን አቃጠለው፡፡
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ንብረቱን እየሸጠ ደሃ እየሆነ ሄደ፡፡ ከዚያም አንድ ቀን በመንገድ እየሄደ ሳለ ጓደኛውን አገኘው፡፡ ጓደኛውም በጣም ሃብታም ሆኗል የሚል ወሬም ሰምቶ ነበርና ጓደኛውን “በጣም ሃብታም ሆነሃል አሉ፡፡ ወደቤትህ መጥቼ ለምን አልጠይቅህም?” አለው፡፡
ጓደኛውም “እሺ” ብሎ ጥሩ ቤቱን መኪናውንና ሃብቱን ካሳየው በኋላ “አሁን ያለኝን ነገር ሁሉ አይተሃል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን አንተን ላይህ አልፈልግም፡፡” አለው፡፡
የአገር ሽማግሌዎችም ጠርቶ “ይህ ሰው ከረጅም ጊዜ በፊት አታሎኝ ሲያበቃ በድህነት ዘመኔ ያልጠየቀኝ አሁን ሃብታም መሆኔን ሲያይ መጥቶ ሊጎበኘኝ ይፈልጋልና እናንተ ያገር ሽማግሌዎች ሁለተኛ ወደቤቴ እንዳይመጣ ከልክሉልኝ፡፡” አላቸው፡፡
ሽማግሌዎቹም ታሪኩን ሰምተው ሰውየው በሎተሪ ቲኬቱ የተታለለ መሆኑን በመረዳት ሁለቱ ጓደኛማቾች ሁለተኛ እንዳይተያዩ በሚል ፍርዳቸውን ሰጡ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|