ሌቭና ዋሎክ
በማርቆስ ዳመነ የተተረከ
በአንድ ወቅት ሌቭና ዋሎክ የተባሉ ሁለት ጓደኛሞች ነበሩ፡፡ ሌቭ በጣም ተንኮለኛና ፈጣን ሲሆን ሰዎች ላይ መቀለድ ይወድ ነበር፡፡
አንድ ቀን ከእቅልፉ ነቅቶ ዋሎክን እንዲህ አለው “እናቶቻችን አስቀያሚ አሮጊቶችና አስቸጋሪዎች ስለሆኑ ለምን አናስወግዳቸውም?”
ከዚያም ሌቭ ወደቤቱ ሄዶ እናቱን ወስዶ ወንዝ ካሻገራት በኋላ እዚያው ደብቋት አንድ የግንድ ቁራጭ ይዞ ወደቤቱ በመመለስ ግንዱን ይደበድብ ጀመር፡፡ በዚህን ጊዜ ዋሎክ ሌቭ እናቱን ደብድቦ እየገደላት ነው ብሎ በማሰብ ሄዶ እናቱን ገደላት፡፡
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሌቭ ወደ ደበቃት እናቱ ዘንድ ሄዶ በጣም የሚጣፍጥ የሰሊጥ ቆሎ ሰጠችው፡፡ ሰሊጡንም ይዞ ወደቤቱ በመመለስ ሰሊጥ የሚመስል ሌላ ጥቁርና በጣም መጥፎ ጥሬ አዘጋጀ፡፡
መጥፎውንም ጥሬ ለዋሎክ ሰጥቶት “ይህ ሰሊጥ ነው፡፡ እኔም እየበላሁት ስለሆነ አንተም ብላ፡፡” አለው፡፡
በዚህ ዓይነት በመጠራጠር ሰሊጡን የሰራችው የሌቭ እናት ትሆናለች ብሎ አሰበ፡፡ እናም ሊፈልጋት ሄደ፡፡
ወንዙንም በተሻገረ ጊዜ እንዳልሞተች አወቀ፡፡ ሌቭ ስለቀለደበት በጣም ተበሳጭቶ የእሱንም እናት ከገደላት በኋላ የሙት ሰው ፈገግታ እንዲኖራት አድርጎ ዛፍ ላይ አስቀመጣት፡፡
ሌቭም እናቱን ሊፈልጋት በሄደ ጊዜ ከሩቅ ፈገግታዋን አየ፡፡
ከዚያም “እባክሽ እናቴ ፈገግ አትበይ ምንም አላመጣሁልሽም፡፡” አለ፡፡
ሆኖም እየቀረባት በሄደ ጊዜ በርግጥም መገደሏን አየ፡፡ ይህንን የሰራው ዋሎክ እንደሆነ ቢያውቅም ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ ገባው፡፡ የእናቱን አስከሬን ለተንኮል ሊጠቀምበት አስቦ ወደ መንደሩ ይዟት በመመለስ ከዛፉ ጋር አሰራት፡፡
ከዚያም ወደ መንደሩ በመዝለቅ እጅግ በጣም ውቧን ልጃገረድ እናቴ እዚያ ዛፍ ስር ናት፡፡ “እባክሽ ሄደሽ ትንባሆ የምታጨስበትን ፒፓ ስጫት፡፡ እምቢ ብላ ክፉ ነገር ከተናገረችሽ ግን ምቻት፡፡” አላት፡፡
ስለዚህ ወጣቷ ልጅ ፒፓውን ይዛ በመሄድ ለአሮጊቷ ስትሰጣት መልስ ስላጣች ደብድባት ተመለሰች፡፡
ስትመለስም ምን እንደተከናወነ ጠየቃት፡፡
እሷም “መልስ ስትነሳኝ ደበደብኳት፡፡” አለችው፡፡
“ከዚያስ ምን አለች?” ብሎ ጠየቃት፡፡
“ምንም መልስ አልሰጠችኝም፡፡” አለችው፡፡
እሱም “እንደዚህ ከሆነማ ገድለሻታል ማለት ነው፡፡ ነይ እስኪ እንያት፡፡” አላት፡፡
ሲሄዱም እናትየው መሞቷን አዩ፡፡
እሱም “እናቴን ስለገደልሻት ካሳ ይሆነኝ ዘንድ አንቺ እኔን ማግባት አለብሽ፡፡” አላት፡፡
በዚህም አይነት ቆንጆዋን ልጅ አግብቶ አብረው መኖሩ ጀመሩ፡፡ ነገር ግን አሁንም በጣም ሰነፍ ስለነበረ ብዙ አላመረተም ነበር፡፡ ስለዚህ በቆሎና የመሳሰሉትን ከሌላ ገበሬ ምርት ላይ ሊሰርቅ ሄደ፡፡
ገበሬውም ሌባ እንደመጣበት ሲያውቅ የዚያን ዕለት ብዙ የሚያጣብቅ ሰምና ሙጫ ዛፉ ላይ ቀባ፡፡ ሌቭም መጥቶ አንድ እጁን ዛፉ ላይ ሲያሳርፍ አጣበቀው፡፡ ከዚያ የተጣበቀውን እጁን በሌላኛው እጁ ሊያላቅቅ ሲሞክር እሱም ተጣበቀ፡፡ ከዚያም እግሮቹን ለመጠቀም ሲሞክር ሙሉ ለሙሉ ስለተጣበቀ የእርዳት ጥሪ ማሰማት ጀመረ፡፡
በዚህ ጊዜ የመንደሩ ሰዎች ሁሉ መጥተው የሞቀ ውሃ ዛፉ ላይ ሲያፈሱለት ሰሙ ስለቀለጠ ለቀቀው፡፡ ከዚያም ሁለተኛ ክፉ ነገር እንዳይሰራ አስጠነቀቁት፡፡
ነገር ግን ሌቭ በቀላሉ የሚስተካከል ሰው አልነበረም፡፡ ጥፋቱን ቢያምንምና ቢፀፀትም ጥሩ ሰው ግን አልነበረም፡፡
እናም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከቤቱ ውጪ ወዳጅ አበጅቶ ልጅ ወለደ፡፡ ልጅ መውለድ መልካም ቢሆንም ከሃጢአቶች ሁሉ የከፋውን አደረገ፡፡
ልጁ የሱ እንዳልሆነ ካደ፡፡ ከቆይታ በኋላም የመንደሩ ሰዎች አባት የሌለው ልጅ በመንደራቸው እንዳለ ተረዱ፡፡
ስለዚህ በክብ ዙሪያ ቁጭ ብለው “ልጁ መሃከል ላይ ይቀመጥና ራሱ አውቆ ወደ አባቱ ይሄዳል::” አሉ፡፡
ከዚያም ከተቀመጡ በኋላ ገና ድክ ድክ የሚለው ልጅ አብሯቸው ተቀመጠ፡፡ ከዚያም ወዲያው ‘ደም ይስባል’ እንዲሉ ልጁ ወደ ሌቭ እየሮጠ ሄደ፡፡
በዚህ ጊዜ ሌቭ ፈጠን ብሎ ልጁ ላይ የአንገት ሃብልና የእግር አልቦ በማሰር ልጁ አባት እንዳለው በማሳወቅ ሌሎች ሳይበሳጩበት ሮጦ ሄደ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|