የአንበሳው ዘፈን
በአላሚ አክውር የተተረከ
አንዲት ከሴት አያቷ ጋር የምትኖር ልጃገረድ ነበረች፡፡ ታዲያ አንድ ቀን የመንደሯ ወጣቶች ወደ ሌላ መንደር ለመጫወት ሲሄዱ የእርሷ አያት “እህሉን ፈጭተሸ ከጋገርሽ በኋላ ነው የምትሄጂው፡፡” አሏት፡፡
ሌሎች ወጣቶች ሲሄዱ እርሷ ለአያቷ ሁሉንም ሥራ ሠራችላቸው፡፡ ማብሰሉን ስትጨርስም አያቷ “አሁን ምግብ ብዪ፤ ካለበለዚያ መንገድ ላይ ይርብሻል፡፡” አሏት፡፡
እናም በላች ነገር ግን ሁሉም ጥለዋት ሄደዋል፡፡ ከዚያም ብቻዋን ወደ መንደሩ እየሄደች ሳለ መንገዷ ላይ አንድ አንበሳ አገኘች፡፡ አንበሳውም እንዳይበላት የሚከተለውን ዘፈን ዘፈነችለት፡፡
“አንበሳ ሆይ፣ ስትበላኝ ኋላዬን ብቻ ብላ
ፊት ለፊቴን ለኦላንግ ልጆች ተውላቸው
የኦላንግ ልጆች ከበሮ እየመቱ ነው
አጉታ ንዲማሩም ከእርሱ አንዱ ነው
ከበሮ መምታት ስለማይችል ወደ ጨዋታው አልሄደም
ዛሬ በአንበሳው ይበላል”
አንበሳውም “አዎን አንቺን በኋላ እበላሻለሁ፡፡” አላት፡፡ ከዚያም አንበሳው እየተከታተላት እርሷ እየዘፈነችለት ከመንደሩ አጠገብ ደረሱ፡፡
ፍቅረኛዋም ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ድምጿን ስለሰማ ተዘጋጅቶ በመምጣት አንበሳውን በጦር ወጋው፡፡
አንበሳውም ሲወድቅ እንዲህ አለ “እባክህ እንደገና ውጋኝ?” ፍቅረኛዋም “ለምን? ፍቅረኛዬን በልተሃት ቢሆን ኖሮ እንደገና ትበላት ነበር?” አለው፡፡
የልጅቷ ዘፈን ትርጉም “ከኋላዬ ብላኝ ከፊቴ ሳይሆን ፍቅረኛዬ ፊቴን አይቶ ይለየኝ ዘንድ” ማለት ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|