አቾክና እናቱ
በቻሜ ክዌር የተተረከ
እናቶቻቸው እህታማቾች የነበሩ ሁለት የአክስት ልጆች ነበሩ፡፡ አብረውም ይኖሩ ነበር፡፡ አንደኛው አቾክ የሚባልና ብልጥና ተንኮለኛ ነበር፡፡ ሌላኛው ሌሮ የሚባለው ሞኝ ነበር፡፡
አቾክ እናቱ ሌላ ቦታ እንድትኖር ይዟት ከሄደ በኋላ ለአክስቱ ልጅ “እኔ እናቴን ገድያታለሁ፡፡ ያንተን እናት ደግሞ እንግደላት::” ብሎ አታለለው፡፡
የሌሮ እናት በተገደለችበትም ወቅት ልጆቿ የምትመግባቸው እናት ስለሌላቸው ሲቸገሩ አቾክ ግን እናቱ ወደ ተደበቀችበት በመሄድ ይበላ ነበር፡፡ የምግብ ሰአትም በደረሰ ጊዜ ቀስ ብሎ ሹልክ ብሎ ደርሶ ይመለስ ነበር፡፡
ሌሮም “የት ነበርክ የአክስቴ ልጅ?” ብሎ ሲጠይቀው እሱም “ዞር ዞር ብዬ ልመለስ ብዬ ነው፡፡” ይለዋል፡፡
ከዚያም መብላት ሲጀምሩ እሱ ስለማይርበው ከምግቡ ላይ ይነሳል፡፡ በዚህም ምክንያት ሌሮ የአክስቱ ልጅ እናቱ ጋ እየሄደ እንደሚመለስ ይገነዘባል፡፡ ስለዚህ አቾክ ምግቡን የት እየበላ እንደሚመጣ ለማወቅ ፈለገ፡፡
በድንገትም ሌሮ የአቾክን እናት አገኛት፡፡
እሷም “አንተ ሌሮ አይደለህምን?” ብላ ጠየቀችው፡፡
“አዎ አክስቴ፤ እኔ ሌሮ ነኝ”
“የአክስትህ ልጅ ሊጠይቀኝ ሲመጣ የት ነበርክ?” ብላ ጠየቀችው፡፡
“እረ እሱ ትቶኝ እየመጣ ነው::” አላት፡፡
እሷም “የአክስትህ ልጅ ሁልጊዜ እየመጣ ሌሮ ሞቷል እያለ ይነግረኝ ነበር፡፡” አለችው፡፡
“እረ አይደለም” አለ ሌሮ “እኔ አልሞትኩም፡፡”
ከዚያም አክስቱ ለሌሮ ምግብ ሰጥታው በልቶ ሲጨርስ አቾክ እንዳታለለውና የእሱን እናት አስገድሎት የራሱን እናት እንደ ደበቃት ተገነዘበ፡፡
ከዚያም ሌሮ በበቀል የአቾክን እናት ገደላት፡፡
ከገደላትም በኋላ ያልሞተች በማስመሰል በግራና በቀኝ አጆቿ ትንሽ ገንፎ አሲዟት አስተካክሎ አልጋዋ ላይ አስተኛት፡፡
አቾክ ተመልሶ ሲመጣ እናቱን ቢያናግራትም መልስ ስላልሰጠችው “እያታለልሺኝ ነው፡፡” ብሎ ሁለቱን የገንፎ ጭብጦች ወስዶ በላቸው፡፡ ከዚያም መሞቷን ሲመለከት ሌላ ተንኮል ማሰብ ጀመረ፡፡
በቁርበትም ጠቅልሏት (በተለመደው የቀብር ስነ ስርአት አፈፃፀም መሰረት) ወደ ወንዝ ዳር ከወሰዳት በኋላ ያልሞተች በማስመሰል ከዛፍ ላይ አስደግፎ አቆማት፡፡
ከዚያም ሌሮን ሄዶ በመጥራት “ዛሬ እናቶቻንን ወደ ወንዙ ውስጥ እንከታቸዋለን፡፡” አለው፡፡
ሊያስሯቸውም በሄዱ ጊዜ አቾክ እናቱን ሳይሆን ስፖንጅ ሲያስር ሌሮ ግን እውነተኛ እናቱን አሰረ፡፡
ሌሮም “ያንተን እናት በፊት እንወርውራት፡፡” አለው፡፡
አቾክ እንዲህ አለ “የምትንሳፈፈው እናት ልጅ ንፁህ ነው፤ የምትሰምጠው እናት ልጅ ግን ቡዳ ነው፡፡”
(አቾክ እናቱን የገደለበት ሌሮ መሆኑን አላወቀም ነበር፡፡)
ሌሮ እንዲህ አለ “ቆይ አንወርውራቸው፡፡”
መጀመሪያ የትኛይቱን እንደሚወረውሩ ሲከራከሩ ሁለት ልጃገረዶች ሲያልፉ አዩአቸው፡፡ አንደኛዋ አንድ አይኗ የታወረ ሲሆን ሌላኛዋ ግን ሁለቱም አይኖቿ ብሩህ ነበሩ፡፡ አቾክም ተጣርቶ “እባካችሁ መጥታችሁ ውሃ ቅዱና ይህችን አሮጊት ሴትዮ ውሃ አጠጧት::” አላቸው፡፡
ልጃገረዶቹም ወደወንዙ ወርደው ለስፖንጁና ለአስክሬኑ ውሃ አመጡ፡፡
ውሃውንም “እባካችሁ ውሃው እነሆ፡፡” ብለው ሰጧቸው፡፡ ነገር ግን አሮጊቷ ሴት መልስ አልሰጠችም፡፡
አቾክም “ደንቆሮ ስለሆነች ግፉዋት፡፡” አላቸው፡፡
ልጅቷም ስትገፋው አስከሬኑ ወደቀ፡፡
አቾክ “ተመልከቺ እናቴን ገደልሻት አይይ! ሃላፊነቱን ስለምትወስጂ ትክሻለሽ፡፡” አለ፡፡
ልጃገረዶቹም በካሳነት ለአቾክ ተሰጡት፡፡
ከዚያም ሌሮን “ሚስቶች ስለሌሉን አንድ አንድ እንካፈላቸው::” አለው፡፡
እናም ቆንጆዋን ለራሱ ወስዶ ግማሽ እውሯን ለሌሮ ሰጠው፡፡ ክፍፍሉም ወንዝ ዳር ተፈፅሞ ወደቤት ሄዱ፡፡
ቤት ሲደርሱም ሁለት ሚስቶችና ሁለት ባሎች ሆነው አብረው ሲኖሩ የአቾክ ሚስት ሥራ እምቢ ብላ የሌሮ ሚስት ግን እህል እየፈጨች በየቀኑ ምግብ ታዘጋጅ ነበር፡፡
ስለዚህ አቾክ ሚስት መለዋወጥ ፈልጎ ቢለዋወጡም ችግሩ እንደገና ተከሰተ፡፡
የሌሮ የቀድሞ ሚስት ሥራ አልሰራም ስትል የአቾክ ሚስት ለሌሮ ጠንክራ መስራት ጀመረች፡፡ ምክንያቱም ሴቶቹና ሌሮ ተንኮሉን አውቀውበት ነበር፡፡
አቾክ አዲሲቱ ሚስት ሥራ አልሰራም ስትለው ሌሮን “እሷ ለእኔ ጥሩ ስላልሆነች ሁለቱንም ውሰዳቸው፡፡” አለው፡፡ ከዚህ በኋላ ሰው ሁሉ ተንኮሉ ስለሰለቸው ከማህበረሰቡ ተወግዶ በገለልተኝነት እየተንከራተተ መኖር ጀመረ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|