ውሻውና ጌታው
በኦኮክ አጁሎ የተተረከ
ውሻ ለአደንና ትንንሽ የዱር እንስሳትን ለመያዝ ስለሚያገለግል በአኝዋክ ማህበረሰብ የተከበረ ነው፡፡ ማታ ማታም ቤት ይጠብቃል፡፡
ከእለታት አንድ ቀን ኦባንግ የተባለ በፓኬዲ መንደር የሚኖር ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው በጣም ጠንካራና የዱር ዓሣማዎችን እያደነ ለዘመዶቹና ለማህበረሰቡ ምግብ የሚያመጣ ውሻ ነበረው፡፡ ይህ ውሻ ታዲያ ወደ ጫካ በተወሰደ ጊዜ የዱር እንስሳ ሳይዝ አይመለስም፡፡
አንድ ቀን ታዲያ ኦባንግ ወደ አደን በሄደ ጊዜ ውሻው ፊት ፊት ሲሮጥ ኦባንግም ተከተለው፡፡ አንድ አንበሣም ድኩላ ሲበላ አገኘው፡፡ አንበሳው ውሻውን ሲያይ ሊገድለው ሲል ውሻው ወደ ኦባንግ ሮጦ ተመለሰ፡፡ ውሻው ኦባንግ አጠገብ ከመድረሱ በፊት አንበሣው ኦባንግን ሳያይ ወደ ምግቡ ተመለሰ፡፡
ኦባንግም “ውሻዬን ያባረረው ማነው?” ብሎ ማንነቱን ለመፈለግ ሄደ፡፡ ኦባንግ አንበሳውን ሲያየው ውሻው አንበሣው ላይ ወጥቶ ስጋውን ሊቀማው ይታገለው ጀመር፡፡ አንበሣውም ተበሳጭቶ ውሻውን ሲያሳድደው ኦባንግ አይቶ መሸሽ ጀመረ፡፡ ሆኖም ውሻው ኦባንግን ወደ ኋላ ትቶ ሩጫውን ቀጠለ፡፡ በዚህ ጊዜ ኦባንግ በውሻውና በአንበሳው መካከል ስለሆነ እንደ ወፍ መብረር ቢቃጣውም አቅቶት ጭቃ ውስጥ ወድቆ ከዚያም ተነስቶ ሽሽቱን ሲቀጥል አንበሳው አሁንም ያሳድደው ነበር፡፡ አንበሳው ሲደርስበት አሁንም ለማምለጥ ሲሞክር ድንገት ወንዙ አጠገብ ካለው ሸንበቆ ውስጥ ወደቀ፡፡ ከዚያም ወንዙ ውስጥ ተንሸራቶ ገብቶ ወደ ጠባቡ አልዎሮ ወንዝ ውስጥ በመዋኘት ተሻግሮ ህይወቱን አተረፈ፡፡
ወደ ቤቱ ሲመለስም ውሻው አደጋ ውስጥ ጥሎት እንደነበር ለሰው ሁሉ በመንገር “እገድለዋለሁ፡፡” አለ፡፡
ዘመዶቹም “ምን ሆነሃል?” አሉት፡፡ ቀጥለውም “ውሻውን አትግደለው ለወደፊት ይጠቅመናል፡፡” አሉት፡፡
እናም አልገደለውም፡፡
በሌላ ጊዜም ውሻውን ይዞ ለአደን ወደ ጫካ ሄደ፡፡ በድንገት አንድ ዘንዶ ኦባንግን ይዞ እላዩ ላይ ተጠምጥሞበት ሊገድለው ሆነ፡፡ ሊሞትም ሲል ውሻው መጥቶ የዘንዶውን ጭራ በመንከስና በመጎተት ከሰውየው ላይ ሲያላቅቀው መሬት ላይ ስለወደቀ ሰውየው ከመጥመልመሉ ሲያገግም ውሻው ዘንዶውን ጎትቶ ጣለው፡፡
ሆኖም ዘንዶው ከጉዳቱ ሲያገግም በድጋሚ ሊይዘው ሲመጣ ኦባንግ ሣንጃውን አውጥቶ በውሻው የተዳከመውን ዘንዶ ገደለው፡፡ ዘንዶውንም በመቆራረጥ ማገዶ ከጫካ አምጥቶ አመድ እስኪሆን ድረስ አቃጠለው፡፡ ወደቤቱ ሲመለስም ውሻው እንዴት እንዳዳነውና ዘንዶውን አመድ እስኪሆን እንዳቃጠለው ለሰው ሁሉ ተናገረ፡፡
ሰዎቹም “አየህ ውሻውን እንኳን አልገደልከው::” አሉት፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|