ማር አዳኞቹ - የጠፋው ነፍስ
በበላይ መኮንን የተተረከ
በአንድ ወቅት የጫካና የዋሻ ማር በመሰብሰብና በመሸጥ ህይወቱን የሚመራ ሰው ነበር፡፡ በዚያ በድሮ ጊዜ በማር ቀፎ ሳይሆን ንቦች ማር የሚሰሩት በጎድጓዳ የዛፍ ግንዶች ውስጥ ነበር፡፡ እናም ይህ ሰው በአንዲት ጠቋሚ ወፍ በመመራት ከጫካ ውስጥ ማሩን ይሰበሰብ ነበር፡፡
ታዲያ አንድ ቀን ንቦች በአንድ ዛፍ ላይ በርከት ብለው ስላየ ማር ሊኖረው ይችላል ብሎ በማሰብ እሳት በመለኮስና እንጨቶቹን በማቃጠል ጭስ አጨሰ፡፡ ከዚያም ጭሱን ከዛፉ ግንድ ውስጥ በማኖር ብዙ ማር ሰበሰበ፡፡ ሆኖም ማሩን የሚይዝበት ስልቻ ስላልነበረው የሰበሰበውን ማር ሁሉ እዚያው ዛፉ ሥር አስቀምጦ ስልቻ ሊያመጣ ይሄዳል፡፡
ነገር ግን ስልቻውን ይዞ ሲመለስ ማሩን በቦታው አላገኘውም፡፡ አንዲት ጃርት በሥፍራው ስታልፍ ማሩን አይታው ኖሮ ሁሉንም ማር በመውሰድ ጓደኞቿን ሰብስባ አብረው ለመብላት ደብቃው ነበር፡፡
ሰውየው ግን ማሩን የወሰደው ሌላ ሰው ነው ብሎ ስላሰበ ይህንኑ ሰው ለመፈለግ ጫካው ውስጥ ሲዘዋወር ወደ አንድ ዋሻ መግቢያ ላይ ይደርስና ከዋሻው ውስጥ ድምፅ ይሰማል፡፡
“ማሬን የወሰደው ሰው እዚህ ውስጥ ነው፡፡” ብሎም አሰበ፡፡ ዋሻው ውስጥም በገባ ጊዜ ዛር የያዛት ሴት አየ፡፡ ሴትየዋም ጠላጠላ ቢራ መሰል ባህላዊ መጠጥ ነው፡፡ ለማዘጋጀት ጥራጥሬዎችን እያነኮረችና ብቅል እየሰራች ነበር፡፡
በሴትየዋ ላይ ያለው ዛርም ሰውየውን “ምንድነው የምትፈልገው?” ብሎ ጠየቀው፡፡
አዳኙም ሰው “ብዙ ማር ሰብስቤ ነበር፡፡ ሆኖም ማሩን የምወስድበት ስልቻ ይዤ ስመለስ ማሩን ከቦታው አጣሁት፡፡ ማሩን የወሰደብኝ ሌላ ሰው ነው ብዬ አስቤ ነበር፡፡ ነገር ግን የአንዲት ጃርት የእግር ዳና እዚህ ዋሻ አጠገብ ስላየሁና ጃርቶችም ጠላቶቼ ስለሆኑ እነርሱን ላጠፋ ነው የመጣሁት፡፡” አለ፡፡
ዛሩም “እነዚህ ጃርቶች ለእኛ ለዛሮች ምግባችን ናቸው፡፡ ልክ እንደ በግና እንደ ፍየል፡፡ ስለዚህ እነርሱን ብትጎዳቸው ክፉ ነገር ይደርስብሃልና ማርህን የሰረቀህን ፈልግ እንጂ እነርሱን እንዳትነካ፡፡” ብሎ አስጠነቀቀው፡፡
ከዚያም ባለ ዛሯ ሴትዮ ቂጣ ሰጥታው ልክ ከዋሻው እንደወጣ እርሱም ወደ ጃርትነት ተለወጠ፡፡ እግሮቹም ከሁለት ወደ አራት ተቀይረው የጃርት እሾህ በሰውነቱ ላይ በቀለ፡፡
ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ዘመዶቹን ፍለጋ ሄደ፡፡ በመንገዱም ላይ ሳለ ሃይለኛ አሳት ስለተነሳ ሰውነቱ ተቃጠለ፡፡ በሰውነቱ ላይ ያለውን የጃርት ፀጉርና እሾህ ከላዩ ተቃጥሎ ሲረግፍ እሱ ወደ ባህሩ ሮጦ ዘሎ ውሃ ውስጥ ገባ፡፡ ከባህሩ ውስጥም በወጣ ጊዜ ወደ ሰውነት ተቀየረ፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ሰውየው በጫካ ውስጥ እየተዘዋወረ ፍራፍሬዎችንና የተፈጥሮ ምግቦችን ከዛፎች ላይ እየተመገበ እንደ ጃርትም እንደ ሰውም ሳይሆን እንደ ጃርትም እንደ ሰውም ሳይናገር መኖር ጀመረ፡፡ በዚህም ምክንያት ጃርትም ሳይሆን ሰውም ሳይሆን ጠፍቶ ቀረ፡፡
እስካሁንም ድረስ እርኩስ ፍጡር ሆኖ ይኖራል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|