የሰው ልጅ አመጣጥ - የመጀመሪያው ሰውና የዝንጀሮ ግልገል
በበላይ መኮንን የተተረከ
አንድ ድሃ ሰው በድህነቱ ምክንያት ወደ ገጠር ሄዶ መኖር ጀመረ፡፡ ዱባና በቆሎ እያመረተም ይኖር ነበር፡፡ ሆኖም ዝንጀሮዎቹ ሰብሉን እየበሉበት ያስቸግሩት ስለነበረ ሰብሉን ከዝንጀሮዎች ለመከላከል ሲል እዚያው ሆኖ ይጠብቅ ነበር፡፡
ከእለታት አንድ ቀን ዝንጀሮዎቹን እያባረረ ሳለ ሁሉም ሸሽተው ሲሄዱ አንዲት ግልገል ዝንጀሮ ብቻውን ወደኋላ ትቀራለች፡፡
ግልገሏም ደስ ስላለችው ወደቤቱ ይዟት ሄደ፡፡ ጓደኛውም አድርጓት ምግብ እየመገባት ባደገች ጊዜ ወደ ማሳው ይዟት ይሄድ ነበር፡፡
ታዲያ እርሱ ዘር በሚዘራበት ጊዜ ትንሿ ዝንጀሮ ከኋላ ኋላው በመሄድ ዘሩን ሁሉ ትበላበት ጀመር፡፡
እርሱም “እንደዚህ አይደለም፡፡ በመጀመሪያ ዘሩ በቅሎ ብዙ እህል ሊኖረን ይገባል፡፡” ብሎ ሲነግራት ምክሩን ሰምታ እንደተባለችው አደረገች፡፡
“ዘሮቹንም እንደዚህ እያደረግሽ ዝሪያቸው፡፡” እያለ አዘራሩንም ያሳያት ነበር፡፡ እንደተባለችውም አደረገች፡፡
በዚህም አይነት ሰብሉ አድጎ አንዳንድ ጊዜ በአረም ወቅት እያገዘችው አብረው ይኖሩ ነበር፡፡
ለአካለ መጠን ስትደርስም ፆታዋ ሴት ነበርና ሰውየው ስለተገናኛት የወለደችው ልጅ አባቱን የሚመስልና በሁለት እግሩ የሚሄድ ነበር፡፡
ሁለተኛውንም ልጅ ወልደው አብረው እየሰሩ መኖር ጀመሩ፡፡ ከሁለቱ ልጆች ታዲያ የመጀመሪያው ወንድ ሲሆን ሁለተኛዋ ልጅ ሴት ነበረች፡፡ ሁለቱም ልጆች ባደጉ ጊዜ እርስ በርስ ተጋብተው የቤተሰቡ ቁጥር ወደ አራት ስላደገ ስራቸውም በጣም እየተስፋፋ ሄደ፡፡
የልጅ ልጆቻቸውም እርስ በርስ እየተጋቡና እየተዋለዱ ዝንጀሮነታቸውን በመተው እንደሰው በጣም በደስታ አብረው መኖር ጀመሩ፡፡
< ወደኋላ |
---|