መነሻ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ገበሬው
ገበሬው
በፋጢማ አሊ የተተረከ
አንድ በሬ ብቻ የነበረው አንድ ድሃ ገበሬ ነበር፡፡ ታዲያ ሌላ አጣማጅ በሬ ተውሶ ለማረስ በጠየቀ ጊዜ ሁሉም ይከለክሉት ነበር፡፡
“አንተ ልመና ብቻ ነው የምታውቀው፡፡” ይሉት ነበር፡፡
ከእለታት አንድ ቀን በእርሻ ላይ ሳለም በእንስራ ሙሉ ወርቅ ያገኝና ይደብቀዋል፡፡ ከዚያም የበሬውን ሸኮና ቆረጠው፡፡ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው “ይህን ለምንድነው ያደረከው?” ብለው ሲጠይቁት “አልፈልገውም ለድሆችም ይሁን” አላቸው፡፡ እነርሱም “አንተም ድሃና በቤትህ ውስጥ የምትበላው የሌለህ ሆነህ እንዴት እንዲህ ታደርጋለህ?” አሉት፡፡
እርሱ ግን ድርጊቱን ገፍቶበት ሲያበቃ “በሬውን እግዚአብሔር ስለሰጠኝ አሁን ደግሞ ለድሆች ምግብነት ይዋል፡፡” ብሎ መለለሰላቸው፡፡ ሁኔታው ግራ ቢገባቸውም በሬውን አርደው ለድሆች አከፋፈሉት፡፡
ገበሬውም ወደ ቤቱ ተመልሶ ሚስቱን “ከረጢት ስጪኝና ተከተይኝ፡፡” አላት፡፡
አብረውም ሄደው ወርቁን ቆፍረው ከወጡ በኋላ ባለፀጋ ሆኖ ሃብት ሞልቶት ለእግዚአብሔር አስራት እያስገባ መኖር ጀመረ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|