ጅብ፣ አንበሣና ቀበሮ
በአብዱራሂም ኢብራሂም የተተረከ
በአንድ ወቅት ሦስት በጣም ጥሩ ጓደኛሞች የነበሩ ጅብ፣ አንበሣና ቀበሮ ነበሩ፡፡ እነዚህ እንስሳትም በጣም ይዋደዱ ስለነበረ ጥሩ አንድነት ነበራቸው፡፡ እርስ በርስ እየተነጋገሩ፣ አብረው እየተጨዋወቱና እየተጋገዙ ይኖሩ ነበር፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ እንስሳ አግኝተው አረዱት፡፡ ሥጋውንም ሶስት ቦታ ሊከፋፍሉት ወሰኑ፡፡ ጅቡ አቡ አሊ፣አንበሳው ጁማአ እንዲሁም ቀበሮው አቡ ሁሴን ይባሉ ነበር፡፡ ጅቡም በጣም በመቆጣትና በስስት ሥጋውን የመከፋፈሉን ሥራ ወሰደ፡፡ በአከፋፈሉም ወቅት አጥንት ስለሚወድ ጥሩ ጥሩ አጥንቶችና ጥሩ ሥጋ ለራሱ አደረገ፡፡ ሥጋውን ማከፋፈሉ እንዳለቀም ሶስቱም የየድርሻቸውን መካፈል ነበረባቸው፡፡ ሆኖም ጅቡ በጣም ስለተንገበገበ ሁለቱን መደብ ለራሱ ወስዶ ሶስተኛውን ብቻ ለሌሎቹ ሲያስቀር እነርሱ በግርምት ይመለከቱት ነበር፡፡
“የእኛስ ድርሻ የታለ? አንተ ሁለቱን መደቦች ወስደህ የቀረው አንድ ብቻ ነው:: ለሁለታችን የሚሆን ድርሻ የታለ?” አሉት፡፡ እሱም “እንደምታውቁት እኔ ትልቅ በመሆኔና ብዙ ስለምመገብ ይህ ልምዴ ነውና ሁለቱን መደቦች ወስጃለሁ፡፡” አላቸው፡፡
“ድርሻችንን ስጠን?” ብለው ቢጠይቁትም አሻፈረኝ አለ፡፡ እነርሱም በጣም ተናደዱ ሆኖም ከአንበሣውና ከቀበሮው ኋላ ሌሎች አንበሶችና ቀበሮዎች ስለነበሩ ጅቡን ቀጥቅጠው ገደሉት፡፡
ሶስቱም መደቦች ስላልተነኩ አንበሳውና ቀበሮው ሥጋውን በሙሉ ለመካፈል ወሰኑ፡፡
አንበሳውም “ስጋውን ማን ያካፍል?” ብሎ ቀበሮውን ጠየቀው በመቀጠልም “አንት ከእኔ የተሻለ ስለ ሥጋ ስለምታውቅ ሥጋውን ቆራርጠህ የማከፋፈሉን ኃላፊነት አንተ ውሰድ፡፡” አለው፡፡
ቀበሮውም ብልህ ነበርና አንበሳው እያየው ሥጋውን ሰባት ቦታ ቆራርጦ አከፋፈለ፡፡
“አንበሣውም እኛ ሁለት ነን፡፡ ሥጋውን ለምን ሰባት ቦታ እንዳከፋፈልከው አልገባኝም?” አለው፡፡
ቀበሮውም መልሶ “ይኸኛው ቁርሴ ይኸኛው ምሣዬ ይኸኛው ደግሞ እራቴ ነው፡፡” ብሎ ሶስቱን መደቦች ወደራሱ ቆጠረ፡፡
“ሌሎቹስ?” አለ አንበሳው፡፡
“እኔ ልንገርህ” አለ ቀበሮው “ይኸኛው ቁርስህ ይኸኛው ምሳህ ይኸኛው ደግሞ እራትህ ነው፡፡” አለው፡፡
አንበሳውም “ሰባተኛው መደብስ?” ብሎ ቀበሮውን ቢጠይቀው ብልሁ ቀበሮ “እንዴት እንዲህ ያለ ጥያቄ ትጠይቀኛለህ? አንተ በጣም ጠንካራ እንስሳ ነህ፡፡ የጅቡንም አሟሟት አይቻለሁ፡፡ ከዚህ በላይ ብወስድ ሞኝነት ነው፡፡ ውድ ጌታዬ ሆይ ሰባተኛው መደብ ያንተ ነው፡፡” ብሎ ራሱን ከሞት አዳነ፡፡
እግዚአብሔርም አንበሳውና ቀበሮው ከዘመዶቻቸው ጋር ሆነው ጅቡን ሲገድሉት ባየ ጊዜ ይህ ደግ እንዳልሆነ በማሰብ ሁሉንም ወደ ዝንጀሮነት ቀየራቸው፡፡ ኃይለኞች ሲበዙ አንድን ሰው ማጥቃት የለባቸውም፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|