

ሰውየውና እባቡ
በአብዱራሂም ባላህ ተተረከ
በድሮ ጊዜ የዱር እንስሳትና የቤት እንስሳት እንደሰዎች ነበሩ፡፡ የሚግባቡበትም ቋንቋ ነበራቸው፡፡ ፀሃፊያችን ብለው የሚጠሩት ገዢም ነበራቸው፡፡ ይህም ፀሃፊ ቀበሮ ነበር፡፡ ቀበሮውም ከሌሎቹ እንስሳት ተለይቶ ለብቻው ይኖር ነበር፡፡ እንስሳቱ በተጣሉ ጊዜ ቀበሮው ዘንድ ሄደው ፍትህ ይሰጣቸዋል፡፡
ታዲያ አንድ ቀን አንድ ሰው ብቻውን እየተጓዘ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ሰዎች እንስሳትን ማናገር ይችሉ ነበር፡፡ ሰውየውም እየተጓዘ ሳለ አንድ እባብ ያገኛል፡፡
እባቡ በእግር መሄድ የማይችል አሳዛኝ ፍጡር ሲሆን ሰውየው ግን ይህን ማድረግ ስለሚችል እባቡም “አንተ ወደፈለክበት መሄድ ትችላለህ፡፡ እኔ ግን ሽባና መራመድ የማልችል ስለሆነ እባክህ ተሸከመኝ?” ብሎ ለመነው፡፡
ሰውየውም እባቡን ተሸክሞ ይጓዝ ጀመር፡፡
ከረጅም ጉዞም በኋላ ሰውየው “አሁን ደክሞኛል፡፡ ብዙ መንገድም ስለተጓዝን እባክህ ውረድልኝ፡፡ እዚህ ትቼህም እሄዳለሁ፡፡” አለው፡፡
ነገር ግን በዚህ ተጣሉ፡፡
እባቡም “አልወርድልህም” አለው፡፡
ሰውየውም “ውረድ” ብሎ ሲጠይቀው “አልወርድም፡፡ እንዲያውም እነድፍሃለሁ፡፡” ብሎ አስፈራራው
እባቡም ወደ ሰውየው ፊት ዞሮ ምላሱን በማውጣት እንደሚነድፈውና እንደሚመርዘው ነግሮት ስላስፈራራው ሰውየው ከፍራቻው የተነሳ እባቡን ተሸክሞ ጉዞውን ቀጠለ፡፡
በዚህን ጊዜ ሰውየው አንድ ሃሳብ መጥቶለት “ለምን ወደ ዳኞች አንሄድም?” አለው፡፡
ከዚያም ወደ ዝሆን፣ ጎሽ እና ወደሌሎች ትልልቅ እንስሳትና ወደ አንበሳና ነብር ተያይዘው ሄዱ፡፡ ነገር ግን እንስሳቱ ዘንድ በደረሱ ጊዜ እባቡ ሁሉንም አንድ በአንድ እነድፋችኋለሁ ብሎ ስላስፈራራቸው ሁሉም ፈርተውት ነበር፡፡
በዚህ ምክንያት ሰውየው ፍትህ ማግኘት አልቻለም ነበር፡፡ ግራም ስለገባው የተሻለ ዳኛ ለማግኘት ሞከረ፡፡ በመጨረሻም ቀበሮው አለቃቸው መሆኑን ሳያውቅ ወደ እርሱ ሄደ፡፡ በዚህም ጊዜ እባቡ በሰውየው አንገት ዙሪያ ተጠምጥሞበት ነበር፡፡
“እዚህ ድረስ አንገቴ ላይ ተጠምጥሞ ይዤው መጣሁ፡፡ እናም አሁን ውረድልኝ ብለው እምቢ አለኝ፡፡” በማለት ሰውየው ክሱን አቀረበ፡፡
በዚህ ጊዜ ቀበሮው “እንግዲያውማ ይህ ቀላል ነው፡፡ ፍርዱንም እኔ እሰጣለሁ፡፡ ሁለታችሁም ቁጭ በሉ፡፡” አላቸው፡፡
ሁለቱም ከተቀመጡ በኋላ ቀበሮው እንዲህ አለ “አሁን ፍርድ እሰጥ ዘንድ ጥያቄዎች ስለምጠይቅ ሰውየው ብዙ መናገር አለበት፡፡ አንተ ግን አንገቱ ላይ ስለተጠመጠምክ እንዴት መናገር ይችላል? ስለዚህ ካንገቱ ላይ ውረድና እኔም ፍርዱን እሰጣለሁ፡፡”
በዚህን ጊዜ እባቡ ከሰውየው አንገት ላይ ወርዶ አጠገቡ ቁጭ አለ፡፡ በዚህ ጊዜ ቀበሮው ወደ ሰውየው ዞር ብሎ “በል በዱላህ ቀጥቅጠህ ግደለው::” ብሎ መከረው፡፡
ሰውየውም እባቡን ጭንቅላቱን ቀጥቅጦ ከገደለው በኋላ በጣም ደስ አለው፡፡ ቀበሮውንም እንዲህ አለው “ባለውለታዬ ነህ፡፡ ህይወቴንም አትርፈህልኛል፡፡ ምስጋናም ማቅረብ ስላለብኝ አንዲት ግልገል ወይም በግ አመጣልሃለሁና እባክህ እንዳገኝህ ከዚህ የትም አትሂድ?”
በስጦታውም ቀበሮው በጣም ተደስቶ እንደሚጠባበቅ ሲነግረው ሰውየውም በተንኮል ቃሉን ባለመጠበቅ አንድ ውሻ ሸማውሸማ የኢትዮጵያ የባህል ልብስ ሲሆን ወንዶችና ሴቶች የሚለብሱት ከጥጥ የተሰራ ስስ ልብስ ነው፡፡ ስር ደብቆ ይዞ መጣ፡፡ ወደ ቀበሮውም ተጠግቶ ውሻውን ለቀቀበት ውሻና ቀበሮ ባላንጣዎች ስለሆኑ ውሻው የቀበሮውን አንገት በጫጭቆ ገደለው፡፡ ስለዚህም ሰውየው ታማኝነት ጎድሎት የገባውን ቃል አፈረሰ፡፡
ቀበሮው ሊሞት እያጣጣረ “ሰው እንዴት ተንኮለኛ ነው?” ያለውን አባባል ቀበሮዎች ሁሉ እስካሁን ሲያስታውሱት ይኖራሉ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|