ዝንጀሮና ማር
በይርጳ ከበደ የተተረከ
አንድ አንበሣ አንድ ሲኒ ማር ይዞ ይጓዝ ነበር፡፡
አንዲት ዝንጀሮም ወደእሱ ጠጋ ብላ “በጣም ደክሞኛል፡፡ ማሩን እኔ ልያዝልህና አንተ ተሸከመኝ፡፡” አለችው፡፡
አንበሣውም እንደታዘዘው በማድረግ ማሩንና ዝንጀሮዋን ተሸክሟቸው ይጓዝ ጀመር፡፡ በጉዞዋቸው ወቅት ሁሉ ታዲያ ዝንጀሮዋ ማሩን እየበላች ነበር፡፡ ማሩን እየበላች ሳለችም አንድ ጠብታ ማር አንበሳው ላይ ጠብ አለች፡፡
“ማሬን እየበላሽብኝ ነው እንዴ? አንድ ጠብታ ትከሻዬ ላይ ሲያርፍ ተሰማኝ፡፡” ብሎ ጠየቃት፡፡ “ማር አይደለም እንባዬ ነው::” ብላ መለሰችለት፡፡ እሱም “ለምንድነው የምታለቅሺው ታዲያ?” ብሎ ሲጠይቃት “የእናቴ ሞት ነው የሚያስለቅሰኝ፡፡” ብላ መለሰችለት፡፡
እሱም “አይዞሽ ሁላችንም ሟች ነን፡፡ እንስሳት ሁሉ ይሞታሉ፡፡ ይህ አዲስ ነገር አይደለም::” አላት፡፡
በዚህም ጊዜ ማሩ እያለቀ ሄደ፡፡
ዝንጀሮዋም “አሁን አውርደኝና ማርህን ውሰድ” አለችው፡፡
ዝንጀሮዋም እየወረደች ሳለ አንበሳው “ማሬን አምጪ?” ብሎ ጮኸባት፡፡
ሊይዛት ቢሞክርም ብልጥ ስለነበረች ለመዝለል ስትሞክር አንበሳው ጭራዋን ይዞ ቆረጠው፡፡ ሆኖም ወደጫካው ውስጥ ገብታ አመለጠችው፡፡ አንበሳው እየሮጠ ቢከተላትም እየተከተላት እንዳለ ስላወቀች ከመሰሎቿ ዝንጀሮዎች ጋር ተቀላቀለች፡፡
ዘመዶቿንም “ጭራዬ በመቆረጡ እንዴት ቆንጆ እንደሆንኩ አያችሁ?” አለቻቸው፡፡
የሷንም ምክር ተከትለው ሁሉም ጭራዎቻቸውን እንዲቆርጡ መከረቻቸው፡፡
በዚህም ሁኔታ የሁሉንም ዝንጀሮዎች ጭራ ቆርጣ ቆርጣ ጣለች፡፡ አንበሳውም ተጠግቶ ወደ አንድ ጉብታ ላይ በመውጣት “አንዲት ጭራ ቆራጣ ዝንጀሮ አይታችኋል ወይ?” ብሎ ጠየቀ፡፡
እነርሱም “የሁላችንም ጭራ የተቆረጠ ስለሆነ ማናችንም ከማንም አንለይም::” አሉት፡፡
አንበሳውም “ሁላችሁም ወደ እኔ ኑ!” አላቸው፡፡
እነርሱም “የሁላችንም ጭራ ተቆርጧል እኮ” አሉት፡፡
“እንዴት ሊሆን ይችላል? በሉ አሁን ሁላችሁም አንድ በአንድ በፊቴ እያለፋችሁ የበላችሁትንም ሆነ የጠጣችሁትን እያስታወካችሁ አሳዩኝ::” አላቸው፡፡
በዚህም አይነት ዝንጀሮዎቹ ሁሉ አንድ በአንድ የበሏቸውን ፍራፍሬዎች፣ ጥራጥሬዎችና የመሳሰሉትን ሲያስታውኩ አንደኛዋ ዝንጀሮ ግን ሰርቃ የበላችውን ማር በሙሉ አስታወከች፡፡
አንበሳውም “አንቺ ነሻ ማሬን የሰረቅሽው?” ብሎ ይዟት ሄደ፡፡
ከዚያም አንበሳው የጤፍጤፍ በኢትዮጵያ ደጋማ ስፍራዎች የሚበቅል ሰብል ነው፡፡ ጭድ በማሰባሰብ ሊያቃጥላት አስቦ በሞኝነት እሳት ፍለጋ ሲሄድ ብልጢቷ ዝንጀሮ ዘላ ዛፍ ላይ ወጣች፡፡
ብዙ እምቧዮችንም በማሰባሰብ የጤፉ ጭድ ስር አኑራው ተመልሳ ወደ ዛፉ ወጣች፡፡
እንቧዩም በፈነዳ ጊዜ አንበሳው “እኝህ አይኖቿ ናቸው፤ እኚህ ጆሮዎቿ ይሄ ልቧ፣ እኚህ ደግሞ ኩላሊቶቿ፣ እኚህ እጆቿ፣ እኚህ እግሮቿ” እያለ ይቆጥር ነበር፡፡
“የእምቧይ ፍንዳታ የዝንጀሮ ፍንዳታ መሰለህ እንዴ?” ብላ በግጥም ትስቅበት ጀመር፡፡
አንበሳውም ወደ ላይ ቀና ሲል ዛፍ ላይ አያት፡፡
“አላቃጠልኩሽም እንዴ? እዚያ ላይ እንዴት ልትወጪ ቻልሽ?” ብሎ ሲጠይቃት “አንተ ጭዱ ስር አኑረኸኝ እሳት ስትለኩስብኝ በጭሱ ላይ በመንጠላጠል ተንሳፍፌ እዚህ ወጣሁ፡፡ ጭሱም ተሸክሞ ወደዚህ አመጣኝ፡፡ አንተም ታላቅ እንስሳ ነህ፡፡ ይህንኑ ለምን ሞክረህ አታየውም?” አለችው፡፡
እሱም “እውነት? እውነትም ጭሱ ነው ወደዚያ ተሸክሞ ያወጣሽ?” ብሎ ጠየቃት፡፡
“አዎ” አለችው፡፡
“እርግጠኛ ነሽ ጭሱ ነው የተሸከመሽ?”
“አዎ”
“እኔም እሳቱ ውስጥ ብገባ እንደዚያ ይሆናል? ጭሱ ይዞኝ ሊወጣ ይችላል?” ብሎ ለማረጋገጥ ሲጠይቃት “በእርግጥም አዎ” ብላ መለሰችለት፡፡
“ታዲያ እኔስ ካንቺ በምን አንሳለሁ? አንቺ ያደረግሽውንም ለማድረግ ምን ይሳነኛል? ጭድና እሳት አምጥተሽ ለኩሺብኝ፡፡” አላት፡፡
እሷም እንደተባለችው አድርጋ አንበሳውን አቃጥላ ገደለችው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|