የአዲበርጋ ታሪክ
በደምለው በየነ
አንዲት አዲበርጋ የምትባል ቆንጆ ልጃገረድ ነበረች፡፡ አራት ወንድሞችም ነበሯት፡፡ እነርሱም ለአካለ መጠን ሲደርሱ እንደ እህታቸው ቆንጆ ልጅ ማግባት ፈለጉ፡፡ ሆኖም እንደሷ ያሉ ቆንጆ ልጃገረዶች አላገኙም፡፡
ሶስቱ ወንድማማቾች እንዲህ ተባባሉ “እንደ እህታችን ቆንጆ ያልሆኑ ልጃገረዶችን ለምን እናገባለን?” በመጨረሻም ውሳኔያቸውን ለታላቅ ወንድማቸው እንዲህ ብለው አሳወቁት “ለምን አንተ አታገባትም?”
ታላቅ ወንድማቸውም ልጅቷን ሊያገባ በነበረበት ጊዜ አራተኛው ልጅ እግረ ስንኩል ነበር፡፡ ሆኖም እህቱን ይወዳትና እሷም ትወደው ነበር፡፡
ልጅቷም እንስራዋን አዝላ ውሃ ለመቅዳት በወጣች ጊዜ ሶስቱ ታላላቅ ወንድሞቹና እናትየው አብረው በማሴር ውሃውን ቀድታ ስትመለስ በበሩ ከመግባቷ በፊት ታላቅ ወንድማቸው እግሩን በማጋደም እንዳትገባ እንዲከለክላት ወሰኑ፡፡ እሷም “ምነው ወንድሜ ሆይ እግርህን አውርደህ አሳልፈኝና ልግባ እንጂ፡፡” አለችው፡፡ እሱም “እኔ ወንድምሽ አይደለሁም፡፡ ባለቤትሽ ነኝ፡፡” ይላታል፡፡ ሁለተኛውና ሶስተኛው ወንድማማቾችም ይህንኑ ያደርጋሉ፡፡ እሷም እንዲህ በማለት ተመሳሳይ ጥያቄ ትጠይቃለች “ወንድሜ ሆይ ለምን አታሳልፈኝም?” እነሱም እንዲህ ብለው ይመልሳሉ “እኔ ወንድምሽ አይደለሁም፡፡ እኔ የባለቤትሽ ወንድም ነኝ፡፡” እናትየዋም እግሯን ደንቅራ “እኔ እናትሽ አይደለሁም አማትሽ ነኝ፡፡” ትላታለች፡፡
ይህንን ደግሞ ደጋግሞ ካደረጉ በኋላ አራተኛው ልጅ ግን ከእነሱ ጋር ባለመተባበር እግሩን ያወርድላታል፡፡
ከእለታት አንድ ቀንም አካለ ስንኩሉ ወንድማቸው “የእኔ አዲበርጋ ሆይ እባክሽ ተሸክመሽ ሽንት ቤት አድርሽኝ?” አላት፡፡
እሷም ታደርሰዋለች፡፡ ከዚያም አድርሳው እንዳወረደችው እሱ እንዲህ ይላታል “ይህ ጤፍ የሚዘራበት ማሳ ስለሆነ እንደሽንት ቤት ልጠቀምበት አልፈልግም፡፡”
እሷም ራቅ ወዳለ ቦታና ወደ ገብስ ማሳ ትወስደዋለች፡፡
እንደገና “እዚህ ብፀዳዳ ገብሱን አበላሸዋለሁ፡፡” አላት፡፡
ከዚያም ወደ ሩቅ ቦታ ትወስደዋለች፡፡ እሱም “እዚህ አውርጂኝ የኔ አዲበርጋ፡፡ እስከዚህ ድረስ እንድትሸከሚኝ ያደረኩት እንደ ሽንት ቤት የምጠቀምበት ቦታ አጥቼ ሳይሆን አንድ ችግር እንዳለብሽ ስለተሰማኝ ነው፡፡”
“እናስ ችግሬ ምንድነው?” ብላ ጠየቀችው፡፡
“ወንድሞቼ እያደናቀፉሽ ያሉት ቤተሰብ ውስጥ ችግር ስላለ ነው፡፡”
“ምን አይነት ችግር?” ብላ ጠየቀችው፡፡
እሱም ወንድሞቹ ሊያገቧት እንደሚፈልጉ ነግሯት አገር ጥላ እንድትሸሽ ይነግራታል፡፡
እሷም ምክሩን በመቀበል አገር ጥላ ጠፍታ ማንም ሰው ከማይደርስበት በረሃ ውስጥ ካለው ወንዝ ዳር ላይ ባለ ዛፍ ላይ መኖር ጀመረች፡፡
ታዲያ የአንድ ሃብታም ሰው አገልጋይ የሆነች ሴት ወደ ወንዙ ትመጣለች፡፡ እንስራዋን በውሃ እየሞላች ሳለች ያንዲት በጣም ቆንጆ ልጃገረድ ጥላ በወሃው ውስጥ አየች፡፡
እሷም “ይህች ሴት እኔ ነኝ እንዴ?” ብላ አሰበች፡፡ በመቀጠልም “እንዲህ በጣም ያማረ ፊት እያለኝ ለምን ውሃ እቀዳለሁ?” በማለት እንስራዋን ሰብራ ወደቤቷ ተመለሰች፡፡ ሆኖም ጌታዋ እንደሚበሳጭባት ፈርታ ሃሳቧን በመቀየር ሌላ እንስራ ይዛ ወደ ወንዙ ወረደች፡፡ አሁንም ያንኑ ተመሳሳይ ምስል በወንዙ ውስጥ አየችና የቀድሞውን ሃሳቧን በመድገም እንስራዋን አሁንም ሰበረችው፡፡ በዚህም ጊዜ አዲበርጋ ከዛፉ ላይ ሆና ምራቋን ስትተፋባት አገልጋዩዋ ቀና ብላ ተመለከተቻት፡፡
ከዚያም ወደ ቤቷ ሮጣ በመሄድ ለጌታዋ “ጌታዬ ሆይ ቅድስት ማሪያምን የመሰለች በጣም ቆንጆ ልጃገረድ አየሁ፡፡" ብላ ነገረችው፡፡
ሆኖም ጌታዋ ስላላመናት ይዟት በመሄድ አዲበርጋን አያት፡፡ ውበቷንም አደነቀው፡፡
ይህ ባለፀጋ ሰው ሁለት ምንጣፎችንም ይዞ በመምጣት ዛፉ ስር አነጠፋቸው፡፡ ከዚያም በምንጣፎቹ መሃከል ላይ አንድ ጦር ጫፉን ወደላይ በማድረግ ወደላይ ሰካው፡፡
ከዚያም “በመጥፎ ስነምግባርና በሮሮ ከሆነ የመጣሽው፣ ክፉ ነገር አድርገሽ ከሆነ የሸሸሽው፣ ምንም ሳትቸገሪና ሳትበደይ ከሆነ ከቤት የሸሸሽው እዚህ ጦር አናት ላይ ትወድቂያለሽ፡፡ ነገር ግን እዚህ የመጣሽው እንደ ባሪያ በደል ደርሶብሽና አንቺ ግን ጥሩ ልጅ ከሆንሽ ምንጣፉ ላይ ትወድቂያለሽ” አላት፡፡
በዚህም ጊዜ ምንጣፉ ላይ ወደቀች፡፡ ባለፀጋውንም ሰው አግብታ መኖር ጀመረች፡፡ አካለ ስንኩል ወንድሟም ያለችበትን ስለማያውቅ የእህቱን አድራሻ እየጠየቀ በመጓዝ እቤቷ ደረሰ፡፡ አሁን እሷ በጣም ሃብታም ናት፡፡ በጣም ሃብታም የሆነ ሰው ሚስት ስለሆነችና ብዙ ደንገጡሮች ስላላት አዲበርጋ ከቤት አትወጣም ነበር፡፡
አካለ ስንኩሉ ወንድሟም ከደጃፏ ሲደርስ ዛፉን ነቀነቀው፡፡ እሷም “ይህ ሰው ማነው? እስኪ ማንነቱን ተመልከቱ” ብላ ደንገጡሮቹን አዘዘች፡፡
ደንገጡሮቹም “አንቺን የሚመስል ሰው ነው፡፡” አሏት፡፡
እሷም “እኔ ምንም ዘመድ የለኝም፡፡ ማን ሊሆን ይችላል? ያለኝ አንድ ወንድም አካለ ስንኩል ነው፡፡ ስለዚህ እባካችሁ ሄዳችሁ አጣሩልኝ::” ብላ አዘዘች፡፡
ሌላኛዋ ደንገጡር ሄዳ በማየት ተመሳሳይ መልስ ይዛ በመመለስ “ልክ አንቺን የሚመስል፤ ጥሮሶቹ፤ አይኖቹ፤ ወዘተ….” እያለች ዘረዘረችላት፡፡
“እስኪ እኔ ማንነቱን ልየው ምንጣፎችም አምጡልኝ::” አለቻቸው፡፡
በምንጣፎቹም ላይ በመሄድ ስትመለከተው ወንድሟ ሆኖ ታገኘዋለች፡፡ ተቃቅፈውም ተሳሳሙ፡፡
“ና ግባ” ብላው ይዛውም ወደቤት ገባች፡፡
“አሁን ባለቤቴ እቤት የለም፡፡ ነገር ግን ብልህ ሰው ነው፡፡ ከብቶቹን ጠብቅ ሲልህ ግደላቸው፡፡ ግደላቸው ሲልህ ደግሞ ጠብቃቸው፡፡ የእርሱ ትዕዛዝ አሰጣጥ እንደዚህ ስለሆነ የተናገረህን ነገር ተቃራኒውን አድርግ፡፡ ከብቶቹን ውሃ ወደሌለበት በረሃ ይዘህ ሂድ ሲልህ ወደ ወንዝ ይዘሃቸው ሄደህ ውሃ አጠጣቸው፡፡” ብላ መከረችው፡፡
ባሏም በመጣ ጊዜ የሚስቱን ወንድም ተዋወቀው፡፡ እሷም እንዳለችው አዘዘ፡፡
ሃብታሙ ሰው አንድ ስልቻ አውጥቶ ከበጎች፣ከፍየሎች፣ከበሬ፣ ከላምና ከፈረስ ላይ የተሸለተ ፀጉር ከሞላበት በኋላ “ይህንን ይዘህ ወደ መጣህበት በመመለስ ከመንደርህ ስትደርስ ስልቻውን በዱላ ደብድበው” ብሎ አዘዘው፡፡
የአስማት ዱላ ቢጤም ሰጠው፡፡ ወንድምየውም ሃብታሙ ሰው እንዳዘዘው ሲያደርግ ብዙ በሬዎች፣ላሞች፣ፍየሎች፣ በጎችና፣ ፈረሶች እንዲሁም በቅሎዎች ከስልቻ ውስጥ ወጥተው ሃብታም ባለፀጋ ሆነ፡፡ ሰዎችም ተደነቁ፡፡
ወንድሞቹም “እነዚህ ሁሉ ከብቶች ከየት መጡ?” ብለው በመገረም ጠየቁት፡፡
እሱም “እህታችንን፤ አፈላልጌ አግኝቻት ባሏ ይህን ሁሉ ሰጠኝ::” ብሎ መለሰላቸው፡፡
እናም ትልቁ ወንድማቸው ወደሷ ጋ በመሄድ አካለ ስንኩሉ ልጅ ያገኘውን ሃብት ለማግኘት ፈለገ፡፡
አዲበርጋ ቤትም እንደደረሰ ደንገጡሮቹ ተመለከቱት፡፡
“ይህኛውም ሌላኛውም ሰው አንቺን ይመስላል” ብለው ለእመቤታቸው ነገሯት፡፡
እሷም በምሬት “ሌላ ምን ዘመድ አለኝ?” አለች፡፡ በድጋሚም ሄደው ተመልክተው ተመሳሳይ ነገር ነገሯት፡፡
እሷም “አሁንም በድጋሚ ሄዳችሁ አረጋግጡ::” ብላ አዘዘች፡፡
አሁንም ተመሳሳይ መልስ ስላገኘች ወደ ውጪ ወጥታ ስትመለከት እርኩሱን ሰው አየችው፡፡ ከተፋችበትም በኋላ ወደቤት ይዛው ገባች፡፡
ነገር ግን ለአካለ ስንኩሉ የሰጠችውን ምክር ለዚህኛው አልነገረችውም፡፡ ባሏም በመጣ ጊዜ ከብቶቹን ወደበረሃ ወስዶ እንዲገድላቸው ነገረው፡፡
ከዚያም የአንበሳ፣ የዝሆን፣ የጅብና የጎሽ ፀጉር ሸልቶ ዱላ ከሰጠው በኋላ ደብድበው ሲለው ይህንን ባደረገ ጊዜ ብዙ የዱር እንስሳት ከስልቻው ወጥተው በሉት፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|