የዝንጀሮዋ ፍርድ
በይርጳ ከበደ የተተረከ
አንድ እባብ በጉዞ ላይ ሳለ ሊያቋርጠው ያልቻለው ወንዝ አጠገብ ደረሰ፡፡ ወንዙ ዳርቻ ላይ ቁጭ ብሎ ሳለ አንድ ሰው መጣ፡፡
እባቡም “በጎርፉ ምክንያት ይህንን ወንዝ ማቋረጥ አልቻልኩምና እባክህ እርዳኝ” ብሎ ሰውየውን ጠየቀው፡፡
ሰውየውም “እንዴት ልረዳህ እችላለሁ? አለው፡፡”
“ጭንቅላትህ ላይ መቀመጥ እችላለሁ” በማለት እባቡ መለሰ፡፡
ሰውየውም በጣም ደግ ስለነበር እባቡን በጭንቅላቱ ላይ አድርጎ አሻገረው፡፡ ከተሻገሩም በኋላ “በል አሁን ተሻግረሃልና ከጭንቅላቴ ላይ ውረድ” ብሎ እባቡን ቢጠይቀው እባቡም “አይሆንም! አሁን ረፍዶብሃል፣ እንዴት እንዲህ ብለህ ትጠይቀኛለህ?” በማለት በመኩራራት መለሰ፡፡
“አልወርድም እበላሃለው” አለው፡፡
ሰውየውም “ስለረዳሁህ ውለታዬን እንዲህ ነው የምትመልሰው? የደግነት ምላሹ እንዲህ ነው?” አለው፡፡
“አልወርድም፡፡”
“እንግዲያው ወደዳኛ እንሂድ፡፡ ከፈለግህ የሰው ዳኛ ወይም የእንስሳ ዳኛ ዘንድ እንሂድ፡፡” አለው፡፡
ከዚህም በኋላ ወደ አንድ ሰው ሄዱ፡፡
ዳኛውም ሰው “ይህንን ያደረከው በፍቃደኝነት ነው፡፡ ራስህ ላይ እንዲቀመጥ ስለፈቀድክለት ለምን ይወርዳል? የኔ ፍርድ ይህ ነው፡፡” አለ፡፡
ሰውየውም እባቡን በጣም ፈራው፡፡ እንዲህም አለ፡፡ “ከፍ ወዳለ የእንስሳ ዳኛ መሄድ አለብን፡፡”
በዚህ ሁኔታ ለፍርድ ወደእንስሳት በመሄድ ዝንጀሮን፣ ጅብንና ሌሎች ሰዎችን ቢያናግሩም ሁሉም እባቡን በመፍራት ተመሳሳይ ፍርድ ሰጡ፡፡
ሁሉም በአንድ ድምጽ “በፍቃደኝነት ከተሸከምከው እዚያው የመሆን መብት አለው፡፡ ሊበላህም ይችላል፡፡” በማለት ፍርድ ሰጡ፡፡
የመጨረሻዋ ዳኛ አንዲት ዝንጀሮ ነበረች፡፡
ዝንጀሮዋም ችግሩ ምንድነው?” ብላ ጠየቀየች፡፡
ሰውየውም “የሞላ ወንዝ አሻግረኝ ብሎ ስላሻገረኩት ከጭንቅላቴ አልወርድ አለኝ፡፡” አለ፡፡
“አሃ! እንዲዚያ ነው እንዴ?” አለች ዝንጀሮዋ፡፡
“እንግዲያው ፍርዱንም ለመስጠት ባባቶቻችንና በእናቶቻችን ባህል መሰረት ዛፍ ላይ መውጣት አለብኝ፡፡”
ዛፉም ላይ ከወጣች በኋላ
“በእንደዚህ ሁኔታ ፍርድ መስጠት አልችልም፡፡ አንዳችሁ በግራ አንዳችሁ ደግሞ በቀኝ በኩል እንደተለመደው የከሳሽና ተከሳሽ አኳኋን መቆም አለባችሁ፡፡” አላቸው፡፡
ዝንጀሮዋ እንዲህ ባለች ጊዜ እባቡ ዝንጀሮዋም በተመሳሳይ ሁኔታ እንደሌሎቹ የምትፈራው መስሎት ከሰውየው አናት ወርዶ አጠገቡ ቆመ፡፡
ዝንጀሮዋም እንዲህ አለች፡፡
“በእጅህ ዱላ አልያዝክም እንዴ?”
“በልብህስ ድፍረት የለህም እንዴ?”
“ለምን አንድ ነገር አታደርግም?”
ሰውየውም እንዲህ አለ “ይህንን በፍጹም አላሰብኩም ነበር፡፡ ይህ ከሰማኋቸው ፍርዶች በሙሉ የተሻለ ነው፡፡”
ይህንንም ካለ በኋላ ዱላውን አንስቶ እባቡን ቀጥቅጦ ገደለው፡፡
ከዚህም በኋላ እባቦች በጫካ ውስጥ መኖር ጀመሩ፡፡ ይህም በፍራቻ ጉድጓድ ውስጥ እንዲኖሩ ያስተማራቸው አጋጣሚ ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|