ጃሂቲ
በደምለው በየነ የተተረከ
ሁለት ሴት ልጆች ያለው ሰው ነበር፡፡ የመጀመሪያዋ ሴት ልጁ እናት ስለሞተች ሌላ አግብቶ ሌላ ሴት ልጅ ወለደ፡፡ ሁለቱም ልጆች ለጋብቻ እድሜያቸው ደረሰ፡፡ እናቷ የሞተችባት ልጅ በጥሩ ሁኔታ ያደገች ነበረች፡፡ ስሟም ጃሂቲ ይባላል፡፡ የሁለተኛዋ ልጅ እናት ሃብታም ነበረች፡፡ ጃሂቲም ለጋብቻ እየተዘጋጀች ሳለች ሁለተኛዋ ልጅ ትቀናባት ነበር፡፡
“እኔን ለምን አይድሩኝም? እህቴን ብቻ ለምንድነው ሚያዩት?” ብላ እናቷን ታስጨንቃት ነበር፡፡
እናቷም ትቀና ነበር፡፡ ልጇንም ነጭ ልብስ ታለብሳትና ያንገት ጌጥ፣ የእጅ አምባር፣ ጌጣጌጦችና ጨሌ ታደርግላት ነበር፡፡ ስለዚህ ጥሩ ልብስ ካለበሰቻት በኋላ ወደ ገበያ ልካት ልጃገረዶች እየጨፈሩና ግጥም እየገጠሙ ወደሚውሉበት በመላክ ወንዶች እንዲመርጧት ታደርጋለች፡፡ ጃሂቲን ግን አሮጌና ቆሻሻ ልብሶች ታለብሳት ነበር፡፡
አጋቢዎቹም እንዲህ ብለው ይዘፍኑና ይጨፍሩ ነበር፤
“ጥሩ ልብስ የለበሰችውን እንዳር
ወይስ ቆሻሻ ልብስ የለበሰችውን እንውሰድ?”
እንዲህም እያሉ አንዱ ሌላውን እየተከተለና “ጥሩ ልብስ የለበሰችውን እንዳር…” የሚለውን ዘፈን እየተቀባበሉ ይዘፍኑ ነበር፡፡
ሁለተኛዋም ልጅ ለእናቷ እንዲህ ስትል ነገረቻት፡፡ “ጥሩ ልብስ ለብሼ እንዲያዩኝ አልፈለጉም፡፡ እንዲያውም ቆሻሻ ልብስ የለበሰችውን እህቴን ነው የፈለጉት፡፡”
በዚህም ምክንያት የእንጀራ እናቷ ልጆቹ ልብሳቸውን እንዲቀያየሩ ካደረገች በኋላ ልጇ እንደገና እንድትሞክር ላከቻት፡፡
አጋቢዎቹ ግን እንዲህ እያሉ ይዘፍኑ ጀመር፡፡
“ቆሻሻ የለበሰችውን ልጅ አንፈልግም፡፡
ጥሩ የለበሰችውን ነው የምንፈልገው፡፡”
በዚህም ጊዜ ልጅቷ ወደናቷ ሄዳ እንዲህ አለች፡፡ “ልብሴንም ቀየርኩ እነሱ ግን አሁንም እኔን አይፈልጉኝም፡፡”
እናትየዋም “በይ ሂጂና ሙሽሮች የሚቀመጡበትን ቅጠላማ ቅርንጫፎች ከዛፍ ላይ ገንጥለሽ ይዘሽልኝ ነይ፡፡” ብላ ላከቻት፡፡ የራሷንም ልጅ ጃሂቲ ዛፎቹ ላይ ወጥታ ቅጠሎቹን እንድታደርግ መከረቻት፡፡
“እሷ ቅርንጫፎቹን ስትቆርጥ አንቺ ደግሞ ሃይቁ ዳር ቦታውን አዘጋጂ፡፡ መሬቱም ላይ የሚያዳልጥ የዛፍ ቅርፊት አኑሪና አዳልጧት ሃይቁ ውስጥ ገብታ እንድትሞት አድርጊ፡፡” የዛፉንም ቅርፊት ለጋ ይባላል፡፡
እንደታሰበውም ሆነ፡፡ እህቷ ጃሂቲም ከዛፉ እንድትወርድና አዳልጧት ሃይቁ ውስጥ እንድትወድቅ ባዘዘቻት ጊዜ ሰይጣን ዛፉ ላይ ይዟት ምርኮኛው ስላደረጋት መውረድ አልቻለችም፡፡
በዚህ ጊዜ የሙሽራው ጓደኞች ጃሂቲን ሊወስዷት መጥተው ነበር፡፡ እህትየዋም ወደ ውጪ ስትወጣ ባዩአት ጊዜ “ሙሽራዋ የት አለች?” ብለው ጠየቋት፡፡
“እዚህ የለችም፡፡ ጠፍታለች፡፡” አለቻቸው፡፡
“እነርሱም ምን ማድረግ እንችላለን አሉ?” የተመረጠችውንም ልጅ ባለማግኘታቸው በጣም አዘኑ፡፡ በዚህም ሁኔታ ሰርገኞቹ ወደመጡበት ተመልሰው ሄዱ፡፡ የልጅቷ አባት የወርቅ ነጋዴ ነበር፡፡ ወደቤት ተመልሶ በመጣም ጊዜ “ጃሂቲ የት አለች?” ብሎ ጠየቀ፡፡ ሚስቱም “ወጥታለች እዚህ የለችም” ብላ መለሰችለት፡፡ “ጃሂቲ መምጣት አለባት!” ብሎ በሃይለ ቃል ተናገረ፡፡
ሚስቱም እንዲህ አለች፡፡
“ለምን አትበላም?”
“ለምንስ አትጠጣም? ጃሂቲ ትመጣለች፡፡”
እሱም እንዲህ አለ “ምግብም አልበላም ውሃም አልጠጣም ጃሂቲ እስክትመጣ ምክንያቱም እወዳታለሁ፡፡”
ጃሂቲም ሃይቅ ውስጥ ሆና እንዲህ ብላ መለሰች፡፡
“የሌላኛዋ ልጅ እናት እዚህ ሃይቅ ውስጥ ስለከተተችኝ እንዲበላና እንዲጠጣ ንገሩት::”
የእንጀራ እናቷም ይህንን በማዛባት ላባትየው እንዲህ ብላ ነገረችው፡፡ “ጎረቤት ዘንድ ስራ ስለያዝኩኝ በኋላ መጣለሁ፡፡ አሁን ምግብም ብላ ውሃም ጠጣ” ብላለች፡፡
እሱም እንዲህ በማለት “ጃሂቲ ጃሂቲ የኔ ልጅ እሷ ካልመጣች አልበላምም አልጠጣምም፡፡”
የመንደሩም ልጆች ወደሃይቁ እንደገና በመሄድ እንደናትየዋ መጣራት ጀመሩ፡፡
ጃሂቲም እንዲህ ብላ መለሰች፡፡
“ክፉ ሴት
እናቴ ያልሆነች
ይህን አድርጋብኛለችና
እንዲበላም እንዲጠጣም ንገሩት፡፡”
ሙሽራው በጣም ይወዳት ስለነበር እዛ ባለመኖሯ ትናፍቀው ነበር፡፡ እሱም ከብቶቹን እየጠበቀ ሳለ ሃይቁ ውስጥ አያት፡፡ እሷም መውጣት አቅቷት ነበር፡፡
“እንዴት አድርጌ ላድንሽ እችላለሁ? ብሎ ጠየቃት፡፡”
“ሰይጣኑ ስለያዘኝ ከዚህ መውጣት አልችልም፡፡”
ምግብም ይዞ ነበርና ወደእሷ ወረወረላት፡፡ በየቀኑም እየተመላለሰ እንድትወጣ እንዲህ እያለ ይጠይቃት ነበር፡፡ “እንዴት አድርጌ ላስለቅቅሽ እችላለሁ?፡፡”
እሷም “አትችልም፡፡ ሰይጣኑ ማርኮኛል አለችው፡፡”
በየቀኑም እየተመላለሰ ምግብ ይወረውርላት ነበር፡፡ ነገር ግን እሱ በጃሂቲ ፍቅር የተነሳ እየከሳ ሄደ፡፡
የሱም አባት በዚህ ምክንያት ተጎድተው ስለነበር “ብዙ የሚበላና የሚጠጣ ነገር እያለ ለምንድነው ምትከሳው?” ብለው ሲጠይቁት
“ላንተ መንገሩ ጥቅም የለውም፡፡” ብሎ መለሰላቸው፡፡
እሳቸውም “እባክህ ንገረኝ? ብለው ተማፀኑት፡፡”
በመጨረሻም ልጁ “እጮኛዬ ሃይቅ ውስጥ ገብታብኛለች፡፡ በየቀኑ ባገኛትም ልትወጣ ግን አልቻለችም፡፡ ሁልጊዜ ምግቤንም ስለምሰጣት ለዚህ ነው የከሳሁትና አጥንቴ የገጠጠ የሚመስለው፡፡” አላቸው፡፡
“በል ሄደህ እንዲህ ብለህ ጠይቃት፡፡ እንዴት ላድንሽ እችላለሁ? በምንስ አይነት ልትወጪ ትችያለሽ?” ብለው መከሩት፡፡
ልጁም እንደተባለው ሄዶ ቢጠይቃት እሷም “በሬ አርደህ ትልቅ የስጋ ቁራጭ ወደ ሃይቅ ውስጥ ብትወረውር ሰይጣኑ ያንን አይቶ ይለቀኛል” አለችው፡፡
እንደተባሉትም አደረጉ፡፡ ከጓደኞቹ ጋርም ሄዶ በሬውን በማረድ የኋላ እግሩን ወደ ሃይቅ ውስጥ ወረወሩ፡፡
ስጋውንም በወረወሩ ጊዜ ሰይጣኑ ስጋውን ለመውሰድ ሮጦ ሄደ፡፡ ሆኖም ሌላው ስጋውን ያላየ እውር ሰይጣን ስጋ ያገኘ መስሎት የልጅቷን ጡት ያዘ፡፡ ልጅቷ ብታመልጥም እውሩ ሰይጣን ጡቷን ቦጭቆ አስቀረው፡፡
ከዚህ በኋላ ሁለቱ ተጋብተውና በአንድ ጡትም ቢሆን ልጆችን አፍርተው በደስታ አብረው መኖር ጀመሩ፡፡
ይህንን ታሪክ የሰማነው ከቅድመ አያቶቻችን ነው፡፡
ወደሚቀጥለው > |
---|