ሶስቱ ደንቆሮዎች
በይርጋ እጅጉ የተተረከ
አንድ ደንቆሮ ገበሬ በማረስ ላይ ሳለ በጎች የጠፋባት አንዲት ደንቆሮ ሴት በጎቿን አይቶ እንደሆነ ትጠይቀዋለች፡፡ ሰውየው ደንቆሮ መሆኑን አታውቅም ነበር፡፡
“በጎቼን አይተሃል?” ብላ ስትጠይቀው “ከዚህ እስከዚያ እየዘራሁ ያለሁት ስንዴ ነው፡፡” ብሎ በመጠቆም አሳያት፡፡ እሷም የጠቋሚ ጣቱን አቅጣጫ ተከትላ በመሄድ እንደ እድል ሆኖ የጠፉትን በጎች ስላገኘቻቸው አንደኛውን በግ በምስጋና ትሰጠዋለች፡፡ ሆኖም የስጦታው በግ አንድ እግሩ ሰባራ ነበር፡፡ “በጎቼ ያሉበትን ቦታ ስላሳየኽኝ አመሰግናለሁ፡፡ አንዱንም እግረ ሰባራ በጌን ውሰድ፡፡” አለችው፡፡
እሱም “እባክሽ ሂጂልኝ! ለምንድነው ስራ ምታስፈቺኝ?” አላት::
እሷም ሌላ በግ እንዲሰጣት የጠየቃት መስሏት “አይሆንም! ይኽኛውን ውሰድ::” አለችው፡፡ በዚህም ስላልተስማሙ ወደ ዳኛ ሄዱ፡፡
ሁለቱም ችግሩን በተራ ለደንቆሮ ዳኛ ሲያስረዱ ዳኛውም “ወደድክም ጠላህም ሴትየዋ ያዘለችው ልጅ አንተን ስለሚመስል ልጁ ያንተ ነው፡፡” ብሎ ፈረደ ይባላል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|