የአይጦችና የእንቁራሪቶች ወዳጅነት
በይርጋ እጅጉ የተተረከ
በአንድ ወቅት እንቁራሪቶችና አይጦች ተሰባስበው ስለ ወዳጅነታቸው ከተወያዩ በኋላ በወር አንድ ጊዜ ድግስ በመደገስ መገናኘት ይችሉ ዘንድ የመጀመሪያውን ደጋሽ ለመለየት እጣ ተጣጣሉ፡፡ አይጦቹም እጣ ወጥቶላቸው ለድግሱ መዘጋጀት ጀመሩ፡፡ ድግሱም በጥሩ ሁኔታ ተከናወነ፡፡
የሚቀጥለው ተራ የእንቁራሪቶቹ ነበርና በእጃቸው ላይ ምንም ነገር ስላልነበራቸው በመጨነቅ ምን ማድረግ እንዳለባቸው መወያየት ጀመሩ፡፡ አንደኛውም እንቁራሪት “ምንም የሚያስጨንቅ ነገር የለም:: እንዲያውም እኛ ለየት ያልንና በውሃ ውስጥም ሆነ በምድር ላይ መኖር የምንችል ስለሆነ ለድግሱ ምንም ባይኖረንም አይጦቹን ከውሃ ውስጥ ወዳለው ድግስ ልንጠራቸው እንችላለን፡፡”አለ::
በዚህም አይነት አይጦቹ ወደ ድግሱ ሲመጡ እንቁራሪቶቹ “ኑ ግቡ! ኑ ግቡ!” እያሉ ጮሁ ፡፡ ከአይጦቹም አንዱ “ውሃ ውስጥ እንዴት ልንገባ እንችላለን፡፡ ውሃ ውስጥ ከገባንም እንሞታለን::” አለ፡፡ ከእንቁራሪቶቹም አንዱ ውሃ ውስጥ እንዴት እንደሚዋኝ ባሳያቸው ጊዜ አንደኛው አይጥ “ምንም አዲስ ነገር የለውም፡፡ እንቁራሪቶቹ ይዋኙ የለ እንዴ!?” ብሎ ውሃ ውስጥ ገባ፡፡ ሌሎቹም እንጮቅ! እንጮቅ! ጡብ! ጡብ! እያሉ በገቡ ጊዜ እንቁራሪቶቹ “ጠጡ እንጂ! ጠጡ!” እያሉ ይጠብቋቸው ነበር፡፡ በዚህም አይነት አይጦቹ ሁሉ ውሃ ውስጥ ገብተው ሞቱ፡፡
ስለዚህ ያላቻ ጓደኝነት ይጎዳል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|