የወ/ሮ አይጥና የአቶ ድመት ሰርግ
በይርጋ እጅጉ የተተረከ
በአንድ ወቅት አይጦች ሁሉ ተሰባስበው ችግራቸውን እየተወያዩ ሳለ “አንደኛው ምን ብናደርግ ይሻለናል? ድመቶች ዝርያችንን እየጨረሱ ነው! ”አለ፡፡
ሌሎቹም አይጦች “አይጦችን በድመቶች ከመበላት የሚያድነው ብቸኛው መንገድ ከድመቶች ጋር በጋብቻ መተሳሰር ነው::” አሉ፡፡ ከዚያም አንጋፋ አይጦችን መርጠው ለሽምግልና ወደ ድመቶች ላኳቸው፡፡
ሽማግሌ አይጦቹም “እባካችሁ ጠላትነት ይቅርብን:: ፀባችንን አቁመን በጋብቻ እንተሳሰር፡፡” ብለው ድመቶችን ጠየቁ፡፡
ከድመቶቹም አንዱ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለ::
አይጦቹም “አንዲቷን ሴት አይጣችንን ለአንዱ ወንድ ድመታችሁ ሚስት ትሆነው ዘንድ እንሰጣችኋለን፡፡” አሉ፡፡ በዚህም ተስማምተው የሰርጉ ቀን ተቆረጠ፡፡ ሽማግሌዎቹም ወደ አይጦቹ ተመልሰው ስለሆነው ነገር ሁሉ ሲነግሯቸው አይጦቹ በጣም ተደሰቱ፡፡
በሰርጉም እለት ድመቶቹ ወደ አይጦቹ ቤት እየጨፈሩ መጡ፡፡ እየጨፈሩም እያለ ጭራዎቻቸው ቀጥ ብለው ቆመው ነበር፡፡ አይጦቹም በሩቅ በጥንቃቄ ያዩአቸው ነበር፡፡ ድመቶቹ እንዲህ እያሉ ይዘፍኑ ነበር፡፡
“ቤቷ እዚያ ላይ ነው አንገቷም እንደ ለጋ ዛፍ ነው፡፡” እያሉ እየዘፈኑ ሲመጡ አንዱ አይጥ ይፈራና “እባካችሁ ወደ ቤት ውስጥ ገብተን እዚያ ሆነን እንያቸው፡፡” አለ:: ሌላዎቹ አይጦች “ለምን? ሰርግ አይደለም እንዴ?” ቢሉም አንዳንዶቹ ወደቤት በመግባቱ ስለተስማሙ ወደ ቤት ውስጥ ሲገቡ የቀሩቱ ውጪ ሆነው ሙሽራውን ይጠባበቁ ጀመር፡፡ ድመቶቹ እየጨፈሩ ደርሰው አይጦቹን ዘለው ያዟቸው፡፡ ቤት ውስጥ የነበሩት አይጦች ግን ተረፉ፡፡ እንዲህም አሉ “ይህ እንደሚሆን አውቀን ስለነበር አመለጥን፡፡”
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|