የጋብቻ ሠንሠለት
በይርጋ እጅጉ የተተረከ
በአንድ ወቅት ፍቅራቸውን ሃሳባቸውንና ሁለነገራቸውን እየተካፈሉ የሚኖሩ ባልና ሚስት ነበሩ፡፡ ሆኖም በህይወታቸው አጋማሽ ላይ ሚስትየው ከሌላ ሃብታም ሰው ጋር ወዳጅነት መስርታ ውሽማው ትሆናለች፡፡ አፍቃሪዋም ከባልዋ የበለጠ ሃብታም ስለነበር ባልዋን ፈትታ እንድታገባው ይጠይቃታል፡፡
ሃብታሙም ሰው ትዳሯን እንዴት እንደሚያፈርስ ያቅድ ጀመር፡፡ መጀመሪያ ባልዋ በጣም ውድ እቃዎች እንዲገዛላት እንድትጠይቀው አግባብቷት ባልዋም ገዛላት፡፡ እሷም ወደ ፍቅረኛዋ ሄዳ ይህንኑ ነገረችው፡፡ ፍቅረኛዋም እንደገና ወርቅ እንዲገዛላት እንድትጠይቀው ነገራት፡፡
ሆኖም ባሏ በቂ ገንዘብ ስላልነበረው ገንዘብ ለማግኘት ሲል ስራ ፍለጋ መንከራተት ጀመረ፡፡ በመጨረሻም በቀን ሰራተኝነት ተቀጥሮ ባገኘው ገንዘብ ወርቁን ገዝቶ ወደ ቤት ሲመለስ እሷ ፍቅረኛዋ ጋር ሄዳ ነበር፡፡
ወርቁን ተቀብላው ለፍቅረኛዋ ሄዳ በማሳየት “ተመልከት! ባለቤቴ ገዛልኝ፡፡” ብላ አሳየችው፡፡
እናም ፍቅረኛዋ መሸነፉን ስላመነ በጣም በመናደድና በመቆጣት ሌላ ዘዴ ይፈልግ ጀመር፡፡
ከዚያም እንዲህ አላት “አሁን ሄደሽ ባልሽን ተአምር እንዲሰራልሽ ጠይቂው፡፡” አላት፡፡
እሷም “ምን አይነት ተአምር?” ብላ ስትጠይቀው “ምንም አይነት ተአምር ይሁን፡፡” አላት፡፡
እሷም ተመልሳ ባሏ ይህንን ያደርግ ዘንድ ስትጠይቀው ባሏ በጣም ተጨነቀ፡፡ “ምን ማድረግ እችላለው?” ብሎም እራሱን ጠየቀ፡፡ ጥልቅ ሃሳብ ውስጥ ከገባም በኋላ ጥሏት ሄደ፡፡ በመንገዱም ላይ ለፈጣሪው እንዲህ እያለ ይፀልይ ነበር፡፡ “አምላኬ ሆይ እባክህ ባለቤቴ የምትፈልገውን አይነት ተአምር እሰራ ዘንድ እርዳኝ፡፡”
ከጥቂት ቆይታም በኋላ አምላክ ወደ እርሱ መጥቶ ሁለት በትሮችን ይሰጠውና ፣ሰውየውን በመጀመሪያው በትር ከነካኽው ወደ አህያነት ይለወጣል፣ በሁለተኛው ደግመህ ከነካኽው ተመልሶ ሰው ይሆናል::” ብሎ ነግሮት ሰውየውም በትሮቹን ይዞ ወደ ሚስቱ በመመለስ “አሁን ተአምር ላሳይሽ እችላለሁ::” አላት፡፡ እሷም “ምን አይነት ተአምር?” ብላ ስትጠይቀው “ቆይ ላሳይሽ!” ብሎ በአንደኛው በትር ቢነካት ወደ እንስት አህያነት ተቀየረች፡፡ ከጥቂት ቆይታም በኋላ በሁለተኛው በትር ሲነካት ተመልሳ ወደ ሰውነት ተቀየረች፡፡ ከዚያ በኋላ የመጀመሪያውንና ሰውን ወደ አህያነት የሚቀይረውን በትር ሰጣትና እሷም በትሩን ይዛ ወደ ፍቅረኛዋ አቀናች፡፡
“ባለቤቴ ተአምርን አደረገ እኮ!” ብላ ስትነግረው “ምን አይነት ተአምር?” ብሎ ጠየቃት እሷም “ቆይ ላሳይህ!” ብላው በበትሩ ብትነካው ወደ አህያነት ተቀየረ፡፡
ባልየውም አህያውን እየነዳ ከባድ ጭነት ይጭነው ጀመር፡፡ ጎረቤቶቹም ሃብታሙ ሰው በመጥፋቱ በጣም ተጨነቁ፡፡ ባልየውም አህያውን ለብዙ አመታት በጣም ተገለገለበት፡፡
ጎረቤቶቹ ሃብታሙን ሰው ፍለጋ ላይ ሳሉ ስለሁኔታው ስለተገነዘቡ ብልህ ያገር ሽማግሌዎችን ወደ ባልየው ላኩ፡፡ ባልየውንም አልቅሰው በመለመን አህያውን ወደ ሰውነት መልሶ እንዲቀይረው ተማፀኑት፡፡
ከብዙም ምልጃ በኋላ ባልየው አህያውን በሁለተኛው በትር ነካው፡፡ አህያው በጣም አገልግሎ ስለነበር ወደ ያረጀ ሰው ተቀየረ፡፡ ባልና ሚስቱም ኑሮአቸውን በሰላም መምራት ጀመሩ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|