ቡዳው ሰው
በወርቁ አለሙ የተተረከ
በአንድ ወቅት ሁለት ጓደኛሞች በጉርብትና ይኖሩ ነበር፡፡ ሁለቱም አግብተው ልጆች ወልደው ነበር፡፡ የአንደኛው ሰው ሚስት በጣም ቆንጆ ስትሆን የሌላኛው እምብዛም አይነ ግቡ አልነበረችም፡፡ ባሏም ቡዳ ነበር፡፡
ታዲያ አንድ ቀን ቆንጆዋ ሴት በድንገት ታማ ስትሞት ሁለቱ ጓደኛሞች አብረው አዘኑ፡፡ የሁለቱ ቤተሰቦች ልጆችም ጓደኛሞች ስለነበሩ ሁልጊዜ አብረው ይጫወቱ ነበር፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ሁለቱ አባወራ ጓደኛሞች ለጉዳይ ወደ መንገድ ሄደው ሣለ አንዲቷ የቡዳው ሰውዬ ልጅ እናቷን ያጣችውን ጓደኛዋን ወደ ቤቷ ወስዳ “እናትሽ እኮ እዚህ እኛ ቤት ነው የምትኖረው::” ትላታለች፡፡
እሷም “እሺ አሳይኝ፡፡” ብላት ወደ ቤት ተያይዘው ሲገቡ ጓደኛዋ አንድ ዘንግ ቢጤ ከቤቱ ጣሪያ ስር አወረደች፡፡ በሌላውም ክፍል ውስጥ ብዙ እንስራዎች ነበሩ፡፡ ልጅቷም በያዘችው ዘንግ አንደኛውን እንስራ ብትመታው እንስራው ወደ ጓደኛዋ እናት አስከሬን ተለወጠ፡፡
በመጀመሪያ ልጅቷ በጣም ተደነቀች ከዚያም እናቷን አቅፋ እየሳመች ማልቀስ ጀመረች፡፡
የቡዳውም ሰው ልጅ ጓደኛዋ እናቷን ስላየች ከዚህ ቤት አትወጣም ብላ ስለሰጋች አስከሬኑን በዘንጉ ስትመታው ተመልሶ ወደ እንስራነት ተለወጠ፡፡
እናት አልባዋም ልጅ ወደቤቷ እየሮጠች ሄዳ ያየችውን ሁሉ ለአባቷ ነገረችው፡፡ በመጀመሪያ አላመናትም ነበር፡፡ ከዚያም ያምናትና እንስራውን እንዴት ወደራሱ ቤት ማምጣት እንዳለበት ያስብ ጀመር፡፡ እንስራው ትንሽ ለየት ያለና ወደ አንገቱ አካባቢ ሰባራ ነበር፡፡ ምክንያቱም ሟች አንድ ጥርሷ ሰባራ ነበር፡፡
ትንሿ ልጅ ይህንን ሁሉ ስትነግረው አባትየው አንድ ቀን አንድ መላ አገኘ፡፡ ለጓደኛውም እንዲህ አለው “የባለቤቴን ሙት አመት አከብራለሁ፡፡”
ጓደኛውም “ጥሩ ሃሳብ ነው::” አለው፡፡
“ታዲያ አንዳንድ እቃዎች ታውሰኛለህ፡፡” ሲለው “ምን ዓይነት ዕቃ?” ብሎ ጠየቀ፡፡
“ለጠላጠላ ቢራ መሰል የባህል መጠጥ ነው፡፡ መጥመቂያ እንስራ ያስፈልገኛል፡፡”
“እንስራዎቹን መውሰድ ትችላለህ፡፡”
ከብዙ ድርድር በኋላ እንስራዎቹን ሁሉ ወስዶ ከሰባራው እንስራ በስተቀር ሁሉንም ጠመቀባቸው፡፡
ድግሱ ሁሉ ተዘጋጅቶ ዘመድና ጎረቤት ሁሉ ተሰብስቦ ቡዳውም ሰው ጭምር በድግሱ ላይ ታድመው ነበር፡፡ ሁሉም በድግሱ እየተደሰቱ ሣለ ትንሿ ልጅ አባቷን ወስዳ ዘንጉን አሳየችው፡፡ አባትየውም ዘንጉን ሰርቆ ወደቤቱ በመውሰድ እንስራውን ሲመታው ወደ ሞተችው ሚስቱ አስከሬንነት ተቀየረ፡፡ በጣም ተገርሞ እንደገና ሲመታት ወደ እንስራነት ተቀየረች፡፡
በዚህ በጣም ተናዶ ወንድሞቹን ሁሉ ሰብስቦ አስታጠቃቸው፡፡ በድግሱም መገባደጃ ላይ ያንን እንስራ ወስዶ ከዘመዶቹ መሃከል አኖረውና በዘንጉ ሲመታው እንስራው ወደ ባለቤቱ አስከሬንነት መለወጡን አይተው አለቀሱ፡፡ ቡዳው ሰውዬ የሴትየዋን ነፍስ ለይቶ ስላስቀመጠው በፈለገ ጊዜ ወደ አስከሬኗ መልሶ አገልጋዩ ሊያደርጋት ይችላል፡፡ ነፍሷም በእጁ ስለነበር የተሰበሰቡት ሰዎች እንዲመልሳት አስገደዱት፡፡ በመጨረሻም እንዳይገድሉት ፈርቶ ነፍሷን ስለመለሳት እሷም ነፍስ ዘራች፤ ሰውየውም ከመንደሩ ተባረረ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|