ውሻና አህያ
በወርቁ መርሻ የተተረከ
በአንድ ወቅት የአንድ ሰው ንብረት የነበሩ አንድ ውሻና አንዲት አህያ ጓደኛሞች ነበሩ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ታዲያ ውሻው አህያዋን እንዲህ አላት፡፡
“ሌሊት ሌሊት እየጮህኩ የጌታዬን ንብረት መጠበቅ ሰልችቶኛል፡፡”
አህያውም እንዲህ ብላ አማረረች “እኔም ጌታዬ ወደ ገበያ በሄደ ቁጥር ከባድ ጭነት መሸከም ሰልችቶኛል፡፡ ታዲያ ምን ብናደርግ ይሻላል?”
በመጨረሻም ቤታቸውን ጥለው ለመጥፋት ተስማምተው ተሰደዱ፡፡ እየተጓዙም ሣለ በጣም ለምለምና ውሃ ያለው ሜዳ አጠገብ ደረሱ፡፡ አህያዋ የምትበላውና የምትጠጣው ነገር አግኝታ ስትጠግብ ውሻው ምንም አላገኘም፡፡
እናም አህያዋ ከጠገበች በኋላ “አሁን ማናፋት አለብኝ::” አለች፡፡ ውሻውም አህያዋ እንዳታናፋ እንዲህ ብሎ መከራት “ካናፋሽ የመጀመሪያው ድምፅ ጅቡን ይቀሰቅሰዋል፣ ሁለተኛውም ድምጽ ያለንበትን ቦታ ይጠቁመዋል፣ በሶስተኛውም አንቺን ይበላሻል፡፡”
አህያዋም ምክሩን ችላ ብላ አናፋች፡፡ ጅቡም ድምጿን ሰምቶ በመምጣት አህያዋን መብላት ጀመረ፡፡
ጅቡም አህያዋን እየበላ ሳለ ውሻው ሥጋውን እየቆረጠ ያቀርብለት ነበር፡፡ ታዲያ ጅቡ ውሻውን “የአህያዋን ልብ ስጠኝ::” ቢለው ውሻው “አህያዋ ልብ የላትም፡፡ ልብ ቢኖራትማ ኖሮ ባላናፋች ነበር፡፡” አለው ይባላል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|