የነፍሰ ገዳዩ ሚስት
በመስፍን ሃብተማሪያም የተተረከ›
በአንድ ወቅት ብዙ ከብቶች፣በጎች፣ፍየሎች፣ቤቶችና አገልጋዮች የነበሩት አንድ ባለጠጋ ሰው ነበር፡፡ አግብቶም ሁለት ልጆች ነበሩት፡፡ አንዲት በአቅራቢያው በሚገኝ መንደር ከባሏ ጋር የምትኖር ሴት ነበረች፡፡ በጣም ቆንጆ ሴት ነበረች፡፡ ታዲያ ባሏ አንድ ሰው ይገድልና እንዳይያዝ ወደ ጫካ ሲገባ ሚስቱ ያለልጆች ብቻዋን መኖር ጀመረች፡፡
ታዲያ ባለጠጋው ሰው ስለወደዳት እንደ ሁለተኛ ሚስት አግብቷት መኖር ፈለገ፡፡ እናም ሶስት ያገር ሽማግሌዎችን ባለጠጋው ሰው ሊያገባት እንደፈለገ እንዲነግሯት ላካቸው፡፡
እሷም “አይሆንም:: ባሌ ለጊዜው አብሮኝ ባይኖርም አንድ ቀን ወደ እኔ ይመለሣል፡፡ ባይመጣ እንኳን እመንናለሁ እንጂ አላገባም፡፡” አለቻቸው፡፡
ባለጠጋውም ሰው በሴትየዋ እምቢታ በጣም ተረብሾ ዘመዶቹን ማማከር ጀመረ፡፡
እነርሱም “እሷን እሺ ማሰኛ ዘዴ አለ፡፡” አሉት፡፡
“ምን ዓይነት ዘዴ? የሚያስፈልገውን ሁሉ አደርጋለሁ፡፡” አለ፡፡
በመንደሩ ውስጥ አንድ ጠንቋይ ነበርና ዘመዶቹም እንዲህ ሲሉ መከሩት “ይህን ማድረግ ትችላለህ:: አዳምጥ! ወደ ሴትየዋ ዘመዶች ሄደን ገንዘብና ከብቶች ሰጥተናቸው ሴትየዋን ወደ ጠንቋዩ ቤት ይዘዋት እንዲመጡ ካደረግን በኋላ ለጠንቋዩ ጉዳዩን እናስረዳውና እሱ ምን እንደሚያደርግ ያውቃል፡፡ እናም ሴትየዋ “ስለ ጤናሽ ጉዳይ ለምን ጠንቋይ አታማክሪም ማልቀስ ብቻውን ምንም አያደርግልሽም፡፡” ተብሎ ተነገራት፡፡
በመጨረሻም ወደ ጠንቋዩ ሄዳ ሁለትና ሶስት ሥርዓቶች ላይ ከተካፈለች በኋላ ከመጋረጃው በስተጀርባ የተቀመጠው ጠንቋይ ስሟን ጠርቶ “አንቺ ቆንጆ ወጣት ሴት ሆይ፤ ባልሽ ወደ አንቺ ተመልሶ እንደማይመጣ ላረጋግጥለሽ እወዳለሁ፡፡”
“አንቺ ግን ታማሚና ብቸኛ እየሆንሽ ነው፡፡ ጤናሽ ይመለስልሽ ዘንድ ማግባት አለብሽ፡፡ አለበለዚያ ክፉ መንፈስ አባትሽን፣እናትሽን፣ እህቶችሽንና ወንድሞችሽን ይጨርሳቸዋል፡፡” አላት፡፡
በቤተሰቧ ላይ እልቂት እንዲመጣ ስላልፈለገች በሃሳቡ ተስማማች፡፡
“ባልሽ የሚሆነውም ሰው ነጭ ልብስና ነጭ ባርኔጣ አድርጎ በነጭ ፈረስ ላይ ሆኖ በእጁ ጦር ይዞ እሁድ ቀን ጠዋት ከሰሜን ወደ ደቡብ ሲያልፍ ታይዋለሽ፡፡”
ሃብታሙም ሰው እንዲህ እንዲያደርግ ተነገረው፡፡ ከዚያም ነጭ ልብስ፣ ባርኔጣ፣ ፈረስና የመሳሰሉትን አዘጋጅቶ በተባለው ቀን በበሯ በኩል ያልፍና ሽማግሌዎችን ልኮ ተጋቡ፡፡ የቆርቆሮ ቤትም ሰርቶላት በጎች፣ ፍየሎችና የመሣሰሉትን ሰጥቷት በደስታ ይኖሩ ጀመር፡፡
ታዲያ ከእለታት አንድ ቀን የመጀመሪያው ባሏ የተጣለበትን ካሣ ከፍሎ ወደ መንደሩ ተመለሰ፡፡ በዚህም ምክንያት ባለጠጋው ሰው ሁለተኛ ሚስቱንና ያንበሸበሻትን ንብረት አጥቶ እሷም ወደ ቀድሞ ባሏ ተመለሰች፡፡
ባለጠጋውም ሰው “ብዙ ሃብትና ሚስት እያለኝ የሌላ ሰው ሚስት በመፈለጌ ሁሉንም ነገር አጣሁ፡፡” አለ ይባላል፡፡ አሣ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|