በቅሎዋ ዋርዲት
በመስፍን ሃብተማሪያም የተተረከ
አንዲት ዋርዲት የምትባል ቆንጆ በቅሎ በአንድ መንደር ውስጥ ትኖር ነበር፡፡ ጓደኞቿም ሁሉ ይቀኑባት ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ዋርዲት ውሃ ልትጠጣ ወደ ወንዝ በመውረድ ላይ ሳለች ከአንድ ድንጉላ ፈረስ ጋር ከመንገዷ ላይ ትገናኛለች፡፡
ፈረሱም ውበቷን ያደንቅ ስለነበር “እንደምን አለሽ?” ብሎ ሠላምታ ሰጣት፡፡ “እግዚአብሔር ይመስገን! እኔ ደህና ነኝ:: አንተ እንደምን አለህ?”
ፈረሱም “የት እሄድሽ ነው?” አላት፡፡
“ውሃ ለመጠጣት ወደ ወንዝ እየወረድኩ ነው::”
“ዋርዲት ሆይ! ሁልጊዜም በውበትሽ እማረካለሁ፡፡ በጣም ቆንጆ ነሽ:: ላገባሽም እፈልጋለሁ፡፡ እናም የወላጆችሽን፣ የአባትሽንና የእናትሽን ዘር ንገሪኝ፡፡” አላት፡፡
“ይህንን ለምን ማወቅ ፈለግህ?”
“”እንግዲህ አለ ፈረሱ “በባህላችን መሠረት አንድ ፈረስ የእጮኛውን ማንነት ወይም ዘር ማወቅ አለበት፡፡”
እሷም “እናቴ አገረ ገዢው የሚሳፈሯት ያቺ በጣም ቆንጆ ፈረስ ናት::” አለችው፡፡
“አባትሽስ?” ብሎ ጠየቀ ፈረሱ::
ዋርዲትም “እህቴ ቄሱ የሚሳፈሯት ፈረስ ነች፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን ስትሄድ ታያታለህ::” አለችው፡፡
“አባትሽስ ታዲያ? አባትሽን ነው ያልኩሽ::”
ዋርዲት “አክስቴ ደግሞ የመንደሩ አለቃ የሚሳፈሯት እጅግ በጣም ቆንጆዋ ፈረስ ናት፡፡” አለችው፡፡
“አባትሽን እኮ ነው የምጠይቅሽ” ብሎ ፈረሱ ጠይቆ እንዳበቃ አባቷ የሆነው አንድ ያረጀና ከሥራ ውጪ የሆነ አህያ መጣ፡፡ አህያውም ዋርዲትን “እዚህ ምን እያደረግሽ ነው?” አላት፡፡
እሷም ምንም አልመለሰችለትም::
“መልሺልኝ እንጂ! አንቺን የመጠየቅ መብት የለኝም እንዴ?”
አሷም የማታውቅ በመምሰል ዝም አለችው፡፡
ፈረሱም “ይህ አሮጌ አህያ ማነው እዚህ መጥቶ የሚረብሸን? የተጨማደደና ያረጀ አህያ!” አለ፡፡
እሷም “አላውቀውም::” አለች
ፈረሱም “ሂድ ከዚህ!” ብሎ በቡጢ መታው፡፡
አህያውም ሲወድቅ ፈረሱ ደጋግሞ ሲረጋግጠው ሞተ፡፡
ታዲያ ሊሞት ሲል እንዲህ አለ “አምላኬ ሆይ የሆንኩትን አየህ?”
ከዚያ እግዚአብሔርም በቅሎዋን “አንቺ አባትሽን አላከበርሽም፡፡ ስለዚህ አንቺም መሀን ትሆኛለሽ፤ ልጆችም አትወልጅም፡፡” ብሎ ረገማት፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|