ውሻውና የሚያናፋው አህያ
በመጋቢ እንየው ገሠሠ
በአንድ ወቅት አህያና ውሻ አብረው ይኖሩ ነበር፡፡
ታዲያ አንድ ቀን አህያው ውሻውን እንዲህ አለው፡፡ “ሁሉንም ነገር ይጭኑብኛል፡፡ ከባድ ዕቃዎችን ጭምር ሲጭኑኝ የተሸከምኩላቸውን ጭነት እንኳን አያስበሉኝም፡፡ አንተም ብትሆን ቤታቸውን ሌት ተቀን እየጠበክ ከጥቂት አጥንቶች በስተቀር ምንም አይሰጡህም፡፡ ታዲያ ለምድነው ከዚህ ክፉ ጌታችን ጠፍተን ከሌላ ጌታ ዘንድ የማንኖረው?” እናም ተያይዘው ጠፉ፡፡
በመንገዳቸውም ላይ ለምለም ሣርና ውሃ አገኙ፡፡ ውሻው ተኝቶ ሣለ አህያው መብላትና መጠጣት ጀመረ፡፡
አህያው ከጠገበ በኋላ ውሻውን “በዚህ ደስ የሚል ጫካ ውስጥ እባክህ አንድ ጊዜ ላናፋ፡፡” ብሎ አማከረው፡፡
“እባክህ እኔ ፈርቻለሁ፤ አትጩህ፡፡ እኔም ከአደጋ አላድንህም፡፡”
“እባክህ አልቻልኩም”
ከዚያም አህያው ማናፋት ጀመረ፡፡ ጅብም ድምፁን ከሩቅ ሰምቶ የድምፁን አቅጣጫ ያፈላልግ ጀመር፡፡
አህያው አሁንም ሣሩን ጋጥ ጋጥ አድርጎ “እባክህ ልጩህ” አለ፡፡
“የመጀመሪያው ጩኸትህ ያለህበትን ለጅቡ ይጠቁማል እንደገና ከጮህክ ጅቡ ያገኘናልና እባክህ ይቅርብህ፡፡”
“አልችልም፣ አልችልም ሆዴ በጣም ስለጠገበ ማናፋት አለብኝ አለበለዚያ ደስተኛ አልሆንም፡፡” ሲለው ውሻውም “እንግዲያው ግፋበት፡፡” አለው እናም አህያው ለሁለተኛ ጊዜ ሲያናፋ ጅቡ መጥቶ “እዚህ ነው እንዴ ያለኽው? እዚህ መገኘት የለብህም፡፡” ብሎት አህያውን ገደለው፡፡
ጅቡም የቻለውን ያህል ከበላ በኋላ የተኛውን ውሻ አይቶ “አንተስ? ምን እያደረግክ ነው?” አለው፡፡
ውሻውም ስለጉዟቸውና ከጌታቸው ጠፍተው እየሄዱ መሆኑን ለጅቡ ነገረው፡፡
ጅቡም “ያንተ ሥራ ምንድነው?” አለው፡፡
“የጌታዬን ላሞች መጠበቅ፡፡”
“ታዲያ አሁን ምን ልታደርግ መጣህ?” አለው ጅቡ፡፡
“ጌታዬ ያንገላታኛል፤ በቂ ምግብም አይሰጠኝም፡፡ ስለዚህ ከአህያው ጋር ተመካክረን ጥሩ ጌታ እናገኛለን ብለን ወደዚህ መጣን፡፡” አለው፡፡
ጅቡም “እንግዲያው የቀረውን ሥጋ ጠብቅልኝ፡፡” ብሎ ዞር ዞር ብሎ ሲመለስ ውሻው የጠበቀውን ሥጋ አስረከበው፡፡ የአህያው ልብ ግን አልነበረም፡፡
“ልቡ የታለ?” ብሎ ጅቡ ቢጠይቅ ውሻው “ጌታዬ ሆይ አህያው፣ ልብ የለውምበተለምዶ ልብ የብልህነት መገኛ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡፡፡ ከተወለደ ጀምሮ ልብ ኖሮት አያውቅም፡፡ ጅልና ደካማ ነበር፡፡ ልብ ቢኖረውማ ባላናፋ ነበር፡፡” አለው ይባላል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|