ስንዝሮ
በመጋቢ እንየው ገሠሠ
ሰባት ሞኝ ልጆች ያሏቸው ባልና ሚስት ነበሩ፡፡
እናትየው እንዲህ እያለች ትፀልይ ነበር “አምላኬ ሆይ፣ ለምን ሰባት ሞኝ ልጆች ሰጠኸኝ? እባክህ አንድ ብልጥ ልጅ ስጠኝ” እያለችም ተሣለች፡፡
በመጨረሻም አንድ ብልጥ ልጅ ተወለደ፡፡ ልጁም በጣም አጭር ስለነበር ስሙን ስንዝሮ አሉት፡፡ ድንክም ስለነበር እንደ ሴት አንቺ ብለው ይጠሩት ነበር፡፡ እናቱም ይህ ልጇ ሞኝ እንዳይሆንባት በማሰብ ክፉ መንፈሱን ለማታለል ስትል ልጁን “አንቺ” ብላ ትጠራው ጀመር፡፡ ሆኖም በጣም ብልጥ ስለነበር ወንድሞቹ አይወዱትም ነበር፡፡ ያዋርደናል ብለውም ያስቡ ነበር፡፡
ታዲያ ከዕለታት አንድ ቀን ከብቶች ሊሰርቁ ይሄዳሉ፡፡ ላሞች፣ ፍየሎች፣ በጎች ሊሰርቁ ቢፈልጉም አልቻሉም፡፡
“ስንዝሮ አብሮን ቢሆን ኖሮ ምን ማድረግ እንዳለብን ይነግረን ነበር፡፡” አሉ፡፡ ስንዝሮም ይህንን ሲሉ ይሰማቸውና “አለሁ፣ እረዳችኋለሁ፡፡” አላቸው፡፡
እናም ስንዝሮን እንዲህ አሉት፡፡ “በፈለግከው መንገድ በረቱ ውስጥ ገብተህ ሁለት ወፍራም የሚበሉ በሬዎችን ይዘህ ና፡፡”
“እሺ ምንም ችግር የለም፡፡”
ስንዝሮም በጠባብ ቀዳዳ ሾልኮ ገብቶ የበረቱን በር በመክፈት ሁለቱን በሬዎች አመጣላቸው፡፡
በሬዎቹን እየነዱ ስንዝሮም ከኋላቸው እየተከተላቸው ሲሄዱ ባለቤቶቹ መጡባቸው፡፡
ጊዜውም መሽቶ ስለነበር ስንዝሮ የከብቶቹ ባለቤት በመምሰል ጮክ ብሎ እንዲህ አለ “ሁለቱን በሬዎቻችንን አግኝተናቸዋል፤ ተመልሰዋልም፡፡ ይዘናቸው እየመጣን ነው፡፡”
ይህንን ሲሰሙ በሬዎቹን ሊጠብቁ ወጥተው የነበሩት ባለቤቶች ወደቤታቸው ተመለሱ፡፡ እናም በሬዎቹን እየነዱ በመሄድ ላይ ሣሉ የሞላ ወንዝ አጠገብ ደረሱ፡፡ ሰባቱ ሞኝ ወንድማማቾች ወንዙን እንዴት እንደሚሻገሩ ግራ ገባቸው፡፡
“አይይ! ስንዝሮ ቢኖር ኖሮ ምን እንደምናደርግ ያሣየን ነበር፡፡”
ስንዝሮም ገመድ ይዞ መጣ፡፡ ወንዙንም በዋና ከተሻገረ በኋላ አንዱን የገመዱን ጫፍ ከወንዙ ዳር ባለ ዛፍ ላይ አስሮ ሌላኛውን ጫፍ በሌላኛው የወንዙ ዳር ካለው ዛፍ ላይ አሰረ፡፡ በዚህ ዓይነት ዋና የማይችሉት ወንድማማቾች በገመዱ ላይ ተንጠላጥለው ተሻገሩ፡፡
ከዚያም በአንድ ሥፍራ ሲደርሱ አንደኛውን በሬ አርደው ሥጋውን ሲካፈሉ ስንዝሮም ድርሻውን ቢጠይቅ አንሰጥህም አሉት፡፡
“አንተ በጣም ትንሽ ነህ! ሥጋ አያስፈልግህም፡፡”
ስንዝሮም እንዲህ አለ “ቁራጭ ሥጋም ባትሰጡኝ እንኳ ፊኛውን ስጡኝ፡፡”
ፊኛውን ሰጡት፡፡
ስንዝሮም ፊኛውን በመንፋት ዛፍ ላይ ወጥቶ በአርጩሜ ሲገርፈው የጅራፍ ያህል ይሰማ ነበር፡፡
እንዲህም እያለ ይጮህ ጀመር “በሬዎቹን የወሰድኩት እኔ አይደለሁም፣ ወንድሞቼ ናቸው፡፡”
ይህንን ሲሰሙ ሞኞቹ ወንድማማቾች ባለቤቶቹ የመጡ መስሏቸው ሮጠው ሸሹ፡፡ እሱም ሥጋውን ሁሉ በአህያ ጭኖ ወደቤቱ ሄደ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|