በሬና አህያ
በመሰለ ጌታሁን የተተረከ
አንድ በሬ ወደ አንድ አህያ ሄዶ እንዲህ አለው፡፡ “በጣም ሰልችቶኛል፡፡ ያለምንም እረፍት ብዙ እሰራለሁ፡፡ ምን ባደርግ ይሻለኛል?”
አህያውም “እንግዲያው ነገ እንዲህ አድርግ፡፡ በጀርባህ ተኛና አሞኛል፣ ሆዴ ተነፍቷል፣ እያልክ እህ! እህ ብለህ አቃስት” አለው፡፡ በሬውም ይህንን አደረገ፡፡ በሚቀጥለውም ቀን ጌታው መጥቶ እንዲህ አለ “አይይ! በሬዬ ታሟል፡፡ ስለዚህ አህያው ይረስ፡፡” እናም አህያው የበሬውን ስራ በመስራቱ እጅግ ደከመው፡፡
በሬውም ወደ አህያው ጠጋ ብሎ ተጨማሪ ጥሩ ምክሮችን በደስታ ለማግኘት ካጠገቡ አረፍ አለና “ትናትና በጣም ጥሩ ቀን ነበር፡፡ ዛሬም አርፋለሁ፤ ነገም ስራ አልሄድም፡፡ ስለዚህ ገበሬውን እንዴት ማሳመን እንዳለብኝ ንገረኝ፡፡” ብሎ ጠየቀው፡፡ አህያውም “አዬዬ! እንደዚያ ይሻላል ብለህ ነው? ካልሰራህ እንደምትታረድ ሲያወሩ ሰምቻለሁ፡፡” አለው፡፡
በዚህም ምክንያት በሬው ወደ ስራው ለመመለስ ወሰነ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|