ድሃውና ሃብታሙ
በመጋቢ እንየው ገሠሠ የተተረከ
ሁለት ድሃ ጎረቤታማቾች ነበሩ፡፡ እነርሱም አንድ በጋራ የሚጠቀሙበት አህያ ነበራቸው፡፡ ከጊዜ በኋላ አንደኛው ሰው ሃብታም ሲሆን ሌላኛው ድሃ ሆኖ ቀረ፡፡
ሃብታሙም ሰው እንዲህ አለ “አህያውን አርደን እንካፈለው፡፡” ድሃውም “ለምን? ወይ ገንዘቡን ሰጥተኽኝ አህያውን ውሰድ፣ አለበለዚያ እንደቀድሞው አህያውን በጋራ እንጠቀምበት፡፡” አለው፡፡
ባለጠጋውም ሰው “አይሆንም! አህያውን አርደን ሥጋውን ለውሾቼ እወስዳለሁ፡፡ ሥጋውን ለውሾቼ እፈልገዋለሁ፡፡” አለ፡፡
ከዚያም ተያይዘው ወደ አንድ ፍርደ ገምድል ዳኛ ሄደው ሃብታሙ ሰው ክሱን እንዲህ ሲል አቀረበ “ይህ አህያ የጋራችን ነው፡፡ ስለዚህ ገሚሱ የእኔ ድርሻ ስለሆነ መካፈል እፈልጋለሁ፡፡”
ፍርደ ገምድሉም ዳኛ “አዎ! እረዱትና እንደፈለጋችሁ ተካፈሉት::” ብሎ ፈረደ፡፡
አህያውም ታርዶ ሃብታሙ ሰው ግማሹን ሥጋ ለውሾቹ ሲሰጥ ድሃው ሰው አህያው ሲታረድ ከማየት በስተቀር ምንም ማድረግ አልቻለም፡፡
በሌላ ጊዜ ሃብታሙ ሰው ንብረቱን በሙሉ ከቤቱ አውጥቶ “ቤቴን ላቃጥለው ነው፡፡” ብሎ ተናገረ፡፡
“ለምን?” አለ ድሃው ሰው፡፡ “የእኔ ቤት የአንተ ቤት አጠገብ ስላለ አብሮ ይቃጠልብኛል፡፡” አለው፡፡
ፍርደ ገምድሉም ዳኛ “የራሱ ቤት ስለሆነ የፈቀደውን ያድርግ” ብሎ ፈረደ፡፡
በዚህም ሁኔታ ሃብታሙ ሰው የራሱን ቤት ሲያቃጥል የድሃውም ቤት አብሮ ተቃጠለ፡፡
ድሃውም ሰው “ሊከፍለኝ ይገባል” ብሎ ተከራከረ፡፡
ዳኛው “ያንተን ቤት ሊያቃጥል አልሞከረም:: የራሱን ቤት ብቻ ስለሆነ ያቃጠለው ምንም ሊከፍልህ አይገባም፡፡” ብሎ ፈረደ፡፡
ቤቱ የተቃጠለበትም ድሃ ሰው ዛፍ ሥር እየኖረ ቤቱ የተቃጠለበትን ሥፍራ አርሶ ሽንብራ ዘራበት፡፡ ሽምብራውም በቅሎ ማሸት ሲጀምር ሃብታሙ ሰው የነበሩት አራት ልጆች መጥተው የሽንብራውን እሸት በሉበት፡፡
ድሃውም ሰው ወደ ሃብታሙ ሰው ሄዶ “ልጆችህ ሽንብራዬን እየበሉብኝ ስለሆነ ሽንብራዬን መልስልኝ::” ይለዋል፡፡
ሃብታሙም ሰው “እሺ ገንዘብ እሰጥሃለሁ፡፡” አለው፡፡
ድሃው ሰው ግን “ገንዘብ ሳይሆን ሽንብራዬን ነው የምፈልገው፡፡” አለ፡፡
ከዚያም ፍርደ ገምድሉ ዳኛ ዘንድ ሲሄዱ ዳኛው “ሽንብራውን ከፈለገ ሽንብራውን ስጠው፡፡” ብሎ ፈረደበት፡፡
ድሃውም ሰው “አዎ! ጨጓራቸውን ዘርግፌ ሽንብራዬን እወስዳለሁ፡፡” አለ፡፡
ሃብታሙም ሰው ልጆቹ እንዳይገደሉበት በመስጋት ወደ አገር ሽማግሌዎች ሄደ፡፡ ሽማግሌዎቹም ሠላም ለማውረድ ተወያዩ፡፡
ሽማግሌዎቹም እንዲህ አሉ፡፡ “ልጆችህን እንዳይገድል ከፈለግህ የንብረትህን አጋማሽ ልትሰጠው ይገባል፡፡”
በዚህም ዓይነት የከብቶቹን፣ የበጎቹንና የፍየሎቹን ገሚስ ሰጠው ይባላል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|