ነብርና ድኩላ
በመጋቢ እንየው ገሠሠ የተተረከ
ነብርና ድኩላ በአንድ ጫካ ውስጥ አብረው እየኖሩ ሣለ ነብሩ ድኩላውን ለማደን ቢሞክርም አልቻለም፡፡
እናም አንድ ቀን ነብሩ ድኩላውን ጠርቶ እንዲህ አለው “ጓደኛዬ ድኩላ ሆይ፣ እኔን ለምን ትሸሸኛለህ? ባልንጀሮች መሆን እንችላለን፡፡ አንተ የምትበላውን እኔ አልበላም፡፡ የሚያጣለን ምንም ነገር የለም፡፡ አሁን ከእንግዲህ ወዲህ አንተም በህይወትህ ሁሉ እኔን እንዳትፈራኝና እኔም ጓደኛ ልሆንህ እንማማል፡፡”
ድኩላውም በዚህ ተስማምቶ ድኩላው ዛፍ ስር፣ ነብሩ ደግሞ ዛፉ ላይ ይተኛሉ፡፡
ከዚያ በፊት ግን ድኩላው “መሃላው ምን መሆን አለበት?” ብሎ ጠይቆ ነበር፡፡
ነብሩም “አንደኛችን ይህንን መሃላ ብንተላለፍ የወለድነውን ልጅ እግዚአብሔር ይገድለዋል፡፡” ብሎ መልሶለታል፡፡
በዚህም ተስማምተው ድኩላውም ነብሩን ሳይፈራ ኖሮ መወፈርና ነብሩን ማጓጓት ጀመረ፡፡ ነብሩም ወፍራሙን ድኩላ ባየ ጊዜ ጉጉት አደረበት፡፡ መሃላውንም በመስበር ድኩላውን ሊሰለቅጠው ፈለገ፡፡
ነብሩም እንዲህ አለ “የፈለገው ይምጣ እንጂ ስለመሃላው ግድ የለኝም፡፡ ልጄ እንጂ እኔ አልሞት! ልጅ ደግሞ የለኝም፡፡” ብሎ አሰበ፡፡
እናም ነብሩ ድኩላውን ለመያዝ ከዛፉ ዘሎ ሊወርድ ሲሞክር ከዛፉ ቅርንጫፍ ውስጥ ስለተወሸቀ ቅርንጫፉ ሆዱን ወግቶ ይዞ አንጠለጠለው፡፡ ሊሞትም ተቃረበ፡፡
ድኩላውም ዘሎ በመነሣት “ቢአአ፣ ቢአአ” እያለ ነብሩ ላይ ጮኸበት፡፡
ነብሩም እያጣጣረ “ምነው ጓደኛዬ እንደዚህ ሆኜ እያየህ ጥለኸኝ ልትሄድ ነው? መሃላውን ከተላለፍን ልጃችን ይሞታል ብለን ተስማምተን አልነበረም?” አለው፡፡
ድኩላውም “ምናልባት አባትህ ይህንን ዓይነት መሃላ ተላልፎ ባንተ ላይ ደርሶብህ ይሆናል፡፡” አለው ይባላል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|