አልጋ ወራሹ ልዑል
በመሃመድ አህመድ አልጋኒ የተተረከ
በአንድ ወቅት ከብዙ ብዙ አመታት በፊት አንድ ወንድ ልጅ ብቻ የነበረው ንጉስ ነበር፡፡ ንጉሱም ልጁ ጥሩ መሪ እንዲሆን ብዙ ያስብ ነበር፡፡ እንዲህም አለ “ለአንድ ንጉስ አመራር መልካምነት መሰረቱ ትክክለኛዋን ሴት አግብቶ በደስታ መኖር ነው፡፡ ስለዚህ ልጄ አንተም በግዛቴ ተዘዋውረህ በጣም ብልኋን ሴት ፈልግ፡፡”
እናም ታዲያ አንድ ቀን ልዑሉ በመዘዋወር ላይ ሳለ በጣም ቆንጆ የሆነች እረኛ አየ፡፡ ወደ እርሷም ተጠግቶ “ይቅርታ አድርጊልኝ፤ አንድ ግመል ጠፍቶብኝ ነው፡፡ አይተሽው ይሆን?” ብሎ ጠየቃት፡፡ እርኛዋም “አይ ግመል አላየሁም፡፡ ነገር ግን ግመልህ ጭራ የሌለው፣ አንድ አይኑ የጠፋና በቀኝ ጎኑ ላይ ቁስል ያለበት ከሆነ በዚህ በኩል አልፏል፡፡” አለችው፡፡
ልዑሉም “ምን ማለትሽ ነው? ግመሉን ሳታይ እንዴት ልትገልጪው ቻልሽ?” አላት፡፡ እረኛዋም “በተወው ምልክት ማወቅ እችላለሁ፡፡” አለች፡፡
“ምን ማለትሽ ነው?”
እሷም “ተመልከት፣ ይህ ግመሉ የበላው ቁጥቋጦ ነው፡፡ ነገር ግን በቀኝ በኩል ያለውን ብቻ ነው የበላው፡፡ ይህ አንድ አይኑ የጠፋ መሆኑን ሊያመላክተን ይችላል፡፡ ከዚያ ደግሞ ፋንድያውን ተመልከት፡፡ ሁሉም በአንድ ላይ ነው የተከመረው፡፡ አብዛኛውን ግዜ ግመሎች ፋንድያቸውን ሲጥሉ ጭራቸው ስለሚወዛወዝ ወደተለያየ አቅጣጫ ይበትኑታል፡፡ ስለዚህ ይህ ግመል ጭራ የለውም ማለት ነው፡፡ እናም በሶስተኛ ደረጃ ግመሉ አሸዋው ላይ ሲንከባለል ሁልግዜ በግራው በኩል ነው፡፡ ይህ ቀኝ ጎኑ ቁስል ሊኖርበት መቻሉን ያመላክታል፡፡” ብላ ዘረዘረችለት፡፡
ለዑሉም በልጅቷ ብልህነትና እውቀት ተማርኮ ወደ አባቱ በመመለስ “ትክክለኛዋን ሙሽራ አግኝቻለው፡፡” ብሎ ነገረው፡፡
አባትየውም “አዎ ጎበዝ ትመስላለች፡፡ ሄደህ ስለአባቷ አጣራ፡፡” አለው፡፡
የልጅቷም አባት በረሃ ላይ በመጓዝ ላይ ሳለ ልዑሉ ተራ ሰው መስሎ አብሮት ይጓዝ ጀመር፡፡
ጉዞው ረጅም ነበርና ወጣቱ ልጅ ወደ አንጋፋው አባት ዞር ብሎ “ተመልከት፣ ወይ አንተ ተሸከመኝ ወይ እኔ ልሸከምህ እንጂ ጉዞው ረጅም ነው፡፡” አለው፡፡
አባትየውም “ምን አይነት ቀልደኛ ሰው ነህ?” ብሎ ጉዞውን በዝምታ ቀጠለ፡፡
ከዚያም 100 ላሞች ያሉበት መንጋ ዘንድ ሲደርስ ልዑሉ እንዲህ አለ “ይቅርታ አንተ ሽማግሌ፣ እነዚህ ሁሉ ከብቶች የማን እንደሆኑ ታውቃለህ?”
ሽማግሌውም “አዎ አውቃለው፡፡” አሉት፡፡
ልዑሉም “እንዴት ያሳዝናል! ባለቤቱ ድሃ ሰው ነው፡፡” አለ፡፡
ሽማግሌውም እንዲህ ብለው አሰቡ “ይህ ሰው እንዴት ያለ ወዝጋባ ነው? 100 ላሞች ያለው ሰው ሃብታም ሰው መሆን አለበት፡፡”
ጉዞዋቸውን ሲቀጥሉ 11 ከብቶች ማለትም አስር ላሞችና አንድ በሬ ያሉበት ትንሽ መንጋ አዩ:: ልዑሉም “የእነዚህን ከብቶች ባለቤት ታውቃለህ?” ብሎ ጠየቀ፡፡
ሽማግሌውም “አዎ” ብለው መለሱ::
ልዑሉም “በጣም ሃብታም ሰው መሆን አለበት!” አለ፡፡
ሽማግሌውም “ምን አይነት ደደብ ነው!” ብለው ጉዞዋቸውን ቀጠሉ፡፡
ከዚያም ከተወሰነ ግዜ በኋላ ብዙ ጥራጥሬዎችና ስንዴ የተዘሩበት የእርሻ ቦታ ደረሱ፡፡ ልዑሉም “ይቅርታ፣ ነገር ግን ይህንን ስንዴ ማን ሊበላው ይችላል?” ጠየቀ፡፡
ሽማግሌውም እንዲህ አሉ “ምን አይነት ደደብ ነው! ስንዴው የገበሬው ስለሆነ ሌላ ማንም ሰው ሊበላው አይችልም፡፡”
ከዚያም ጉዞዋቸውን እንደቀጠሉ የሞተ ሰው አስክሬን ወደ መቃብር ሲወሰድ አዩ፡፡ ልዑሉም እንዲህ አለ “የዚህ ሰው ስምም አብሮት ይቀበር ይሆን ወይስ እንደገና ይጠራ ይሆን?”
ሰውየውም “ምን አይነት ደደብ ነው! ሰውየው ከሞተ ማንም ሰው ስሙን አይጠራም::” ብለው አሰቡ፡፡
ከዚያም ሽማግሌው በፀጥታ ሲጓዙ ወጣቱ ልጅ ተከተላቸው፡፡
ሽማግሌው ወደጎጇቸው ሲገቡ ልዑሉ ወደ ግቢው ዘለቀ፡፡ በባህሉም መሰረት ሽማግሌው ምንጣፍ ይዘው ወጡ፡፡ ልዑሉ ግን ቢቀመጥበትም እግሮቹን ምንጣፉ ላይ አላኖረም፡፡
ታዲያ አባትየው ልጃቸውን “በጣም ደደብ ሰው ሙሉ ቀን ሲከታተለኝ ውሎ አብሮኝ መቶ ውጪ ነው ያለው፡፡” አሏት፡፡
ስለዚህ ወጣቷ ልጃገረድ ለወጣቱ ልጅ ውሃ ሰጥታው እሱም እግሮቹን ከታጠበ በኋላ ምንጣፉ ላይ አኖራቸው፡፡
ልጅቷም ወደ አባቷ ተመልሳ እንዲህ አለቻቸው “አባባ ይህ ወጣት ልጅ ደደብ ነው ብለህ ነበር፡፡ ነገር ግን ከሚሰራው ነገር አኳያ ልጁ ጎበዝ ይመስለኛል፡፡”
አባትየውም “አይ እሱማ የለየለት ደነዝ ነው፡፡ በመንገድ ላይ ወይ አንተ ተሸከመኝ ወይ እኔ ልሸከምህ አለኝ፡፡ ይታይሽ እኔ በዚህ እድሜዬ እሱን ስሸከመው ከዚያም ብዙ ላሞችን ስንመለከት ባለቤታቸው ድሃ ሰው ነው አለ፡፡ ከዚያም አስር ላሞችና አንድ በሬ ያለበት ትንሽ መንጋ ስንመለከት ባለቤታቸው ሃብታም መሆን አለበት አለ፡፡ ከዚያም በአንድ የስንዴ ማሳ አጠገብ ስናልፍ ስንዴውን በነፃ መብላት ይቻል እንደሆነ ጠየቀ፡፡ ከዚያም አንድ ሰው ሞቶ ሲቀበር ሲያይ ስሙ ከዚህ በኋላ ይነሳ እንደሆን ጠየቀ፡፡ ታዲያ ይህ ሰው ደደብ አይደለም?” አሉ፡፡ ልጅቷም “አይሆንም አባባ ይህ ሰው በጣም የተማረ መሆን አለበት፡፡ ምን ለማለት እንደፈለገ አይገባህም? ተሸከመኝ ሲልህ ጉዞ አሰልቺ መሆኑን ሊነግርህ ፈልጎ ነው፡፡ እናም ወይ ተረት እንድትነግረው ወይም ተረት ሊነግርህ ፈልጎ ነው፡፡ ከዚያም ነገሩ ሁሉ እሱ ትክክል ነበር፡፡ መቶ ላሞች ያሉት ሰው ድሃ ነው ምክንያቱም ኮርማ ከሌለው መንጋው ሞቶ ያልቃል፡፡ አስር ላሞችና አንድ ኮርማ ያለው ሰው ግን መንጋው እያደገ ስለሚሄድ ሃብታም ይሆናል፡፡ ስንዴውም በነፃ ከሆነ ብሎ የጠየቀው ገበሬው ደግና መንገደኞችን ለመመገብ ፍቃደኛ ከሆነ ለማወቅ ፈልጎ ነው፡፡ በመጨረሻም የሞተው ሰው ስም ደግሞ ይነሳ እንደሆነ የጠየቀው ሟቹ ሰው ልጆች አሉት ወይ ብሎ ለመጠየቅ ፈልጎ ነው፡፡ ልጆች ካሉት ስሙ ዘላለማዊ ይሆናል፡፡” ብላ መለሰች፡፡
አባትየውም እንዲህ አሉ “እንግዲያው እሱ እንደዚህ በሚያደናግር መንገድ የሚናገር መሆኑን ከወደድሽለት ለምን አታገቢውም?” አሏት፡፡
ልጅቷም “ምንአልባት አገባው ይሆናል፡፡” ብላ መለሰች፡፡ ከዚያም በመቀጠል “ስፈልገው የነበረው ሰው እንደዚህ አይነት ሰው ነበር፡፡” አለች፡፡
ከዚያም ሁለቱ ለመጋባት ወስነው ልጁ ወደአባቱ ተመልሶ ሄደ፡፡ አባቱም በጣም ተደስቶ በሰርጉ እለት ልጁ ከአጃቢዎቹ ጋር ወደ ሙሽሪት ቤት እንዲሄድ ነገረው፡፡
ነገር ግን ልጁ “አንድ አገልጋይ ብቻ ነው የምፈልገው::” ብሎ መለሰለት፡፡
ልዑሉና አገልጋዩ ወደ ሙሽራዋ ቤት እየተጓዙ ሳለ ውሃ ይጠማቸዋል፡፡ ስለዚህ ልዑሉ ወደውሃው ጉድጓድ ውስጥ ወርዶ ውሃ ሊቀዳ ሲገባ አገልጋዩ እንዲህ አለው “አንድ ምርጫ አለህ፡፡ አንተን ገድዬ ልብስህን ለብሼ ሙሽራህን አገባለሁ፡፡ አለበለዚያ በፍፁም እንደማትነግራት ቃል ከገባህልኝ አንተ አገልጋይ እኔ ደግሞ ጌታ ሆነን መኖር እንችላለን፡፡”
ልዑሉም እንዲህ አለ “እንግዲያው መልካም ከምሞት አገልጋይ ሆኜ ብኖር ይሻለኛል፡፡ ቃልም እገባልሃለሁ፡፡”
በዚህም ተስማምተው ልብሳቸውን፣መሳሪያዎቻቸውንና፣ ሌላውን ነገር ሁሉ ተቀያይረው ወደ ሰርጉ ቤት አመሩ፡፡
ልጅቷ ቀድሞውኑ ልዑሉን አይታው ስለነበረ እንዲህ አለች “ይህ ባለቤቴ አይመስለኝም፡፡”
ሰዎቹ ሁሉ “እርሱ ራሱ ነው፡፡” አሏት፡፡
እሷም “ሶስት ጥያቄዎችን እጠይቀዋለው፡፡ አንደኛው ለወንድ ልጅ እጅግ በጣም ከባድ ሸክሙ ምንድነው? ሁለተኛው እጅግ በጣም ጣፋጩ ምግብ ምንድነው? ሶስተኛው እጅግ በጣም ማራኪው መዓዛ ምንድነው?” አለችው፡፡
አገልጋዩም “እጅግ በጣም ከባዱ ሸክም የወፍጮ ድንጋይ መሸከም ነው፡፡ እጅግ በጣም ጣፋጩ ምግብ ማር ነው፡፡ እጅግ ማራኪው መዓዛ የሽቶ መዓዛ ያለው የስጋ መጥበሻ ቅጠል ነው፡፡” ብሎ መለሰ፡፡
ልጅቷም “ይህ በእርግጥ ባሌ አይደለም፡፡ እስኪ አገልጋዩን ጠይቁት፡፡” አለች፡፡
ልዑሉም እንዲህ ብሎ መለሰ “ለአንድ ሰው እጅግ በጣም ከባዱ ሸክም ለሌላ ሰው ቃል መግባት ነው፡፡ እጅግ በጣም ጣፋጩ ምግብ በረሃብ ግዜ የሚበላ ምግብ ነው፡፡ እጅግ በጣም ማራኪው መዓዛ ደግሞ ህፃን ወንድ ልጅህን ስትስም በአንገቱ ላይ ያለው የቆዳው መዓዛ ነው፡፡”
ልጅቷም እንዲህ አለች “ባለቤቴ ይኽኛው ነው፡፡” እናም በጣም ደስተኛ ሆነው ትክክለኛውን ሰው አገባች፡፡ ነገር ግን ከመጋባታቸው በፊት ሰዎችና እንስሳት ከተመለሱ በኋላ ወደተረተሩ ሁለተኛ በፍፁም እንዳይወርድ ቃል እንዲገባላት አስጠነቀቀችው ምክሯንም ተቀብሎ ቃል ገባላትና በደስታ ተጋብተው ሰባት ወንድ ልጆችም አፍርተው ኖሩ፡፡
ከብዙ ዓመታት በኋላ ልዑሉ ጥጋብ ስለተሰማው የሚስቱን ምክር ረስቶ አንድ ቀን ምሽት ላይ ሁሉም ሰዎችና ከብቶች ወደቤት ከገቡ በኋላ ወደተረተሩ ወረደ፡፡ እዚያም አራት ሽፍታዎች ያዙት፡፡ ሁለቱ ሊገድሉት ሲፈልጉ ሁለቱ ደግሞ ሊለቁት ፈልገው በመጨረሻ በመግደሉ ተስማሙ፡፡
እሱም “ሳትገድሉኝ በፊት አንድ ነገር መናገር እችላለሁ?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡
“አዎ ትችላለህ::”
“እንግዲያው ወደ ቤቴ ሄዳችሁ ሚስቴን ታገኟታላችሁ፣ አሮጊትም ናት፡፡ ስታገኟትም ከላሞቹ መሃከል ጥቁሯ ላም ሌሎቹን እየወጋች አይናቸውንም ስለምትደነቁላቸው መለየት አለባት፡፡ ከዚያም ከቤቴ ጣሪያ ላይ አንድ ጥቁር ምንጣፍ አለ፡፡ እሱንም አውርዳችሁ በነጭ ምንጣፍ ቀይሩት፡፡ ከዚያም ሁለቱን ግመሎቼን እንድትለቃቸውና የቀሩትን ሁለቱን እንድታስቀራቸው ንገሯት፡፡” አላቸው፡፡
በዚህ ተስማምተው ገደሉት፡፡ ነገር ግን ቃል ገብተውለት ስለነበር መልዕክቱን ለሚስቱ ሊነግሯት ሄዱ፡፡
እሷም ሰባቱንም ልጆቿን ጠርታ ካስታጠቀቻቸው በኋላ “እነዚህን ሰዎች ያዟቸው!” ብላ አዘዘች፡፡
ቀጥላም “ስለጥቁሯ ላም የተነገረው የመጀመሪያው መልዕክት ትርጉሙ አባታችሁ አይኑን አሞራ እንዳይበላው መፈለጉን የሚያመለክት ስለሆነ ሄዳችሁ ቅበሩት፡፡ ስለጥቁሩ ምንጣፍ የተነገረው ሁለተኛው መልዕክት ደግሞ በእስልምና ባህል በሃዘን ወቅት ጥቁር ሳይሆን ነጭ ስለሚለበስ እሱ ስለሞተ ነጭ እንድንለብስለት መፈለጉን ያሳያል፡፡ የሶስተኛው መልዕክት ትርጉም ከአራቱ ዘራፊዎች ሁለቱ ብቻ ሊገድሉት መፈለጋቸውን ስለሚያመለክት ሁለቱን ገድለን የቀሩትን ሁለቱን በነፃ እናሰናብታቸዋለን፡፡” አለች፡፡
በዚህም ሁኔታ ሁለቱ ዘራፊዎች ሌሎቹን አስገድደው ባሏን እንዲገድሉ ማድረጋቸውን ራሳቸው ስላመኑ የሰውየው ልጆች ሁለቱን ገድለው የቀሩትን ሁለቱን በነጻ አሰናበቷቸው፡፡
ይህ ተረት ባል ሁልግዜም የሚስቱን ምክር መስማት እንዳለበት ያሳያል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|