ቀበሮና ጅብ
ተራኪው የማይታወቅ
በአንድ ወቅት አንድ ጅብና ቀበሮ አብረውም እየተጓዙ ሳለ በመንገዳቸው ላይ ጅቡ በሬ ሲያገኝ ቀበሮዋ ላም ታገኛለች፣ ቀጥሎም ጅቡ ቢላዋ ሲያገኝ ቀበሮዋ ደግሞ የታሰሩ ሸንበቆዎች ታገኛለች፡፡ ቀበሮዋም እንዲህ አለች “አንዱ ሸንበቆ ቢጠፋብኝ ሌላውን እጠቀማለሁ፡፡ አንተስ፣ ቢላዋው ቢጠፋብህ ምን አማራጭ አለህ?” ብላ ጠየቀችው፡፡
ጅቡም “ሸንበቆዎቹን ስጭኝና ቢላዋውን ሰጥሻለሁ፡፡” አላት፡፡ ቀበሮዋም “እሺ” አለች፡፡
ከዚያ ደግሞ “ላሜን ሳርዳት አትጮህም፡፡ ያንተ በሬ ግን ያጓራል::” አለችው፡፡
ጅቡም “እንግዲያው ላምሽን ስጭኝና በሬዬን ልስጥሽ” ብሎ ጠየቃት፡፡ በዚህም ሁኔታ ተለዋውጠው መሄድ እንደጀመሩ ቤት አገኙ፡፡ ጅቡ ያገኘው ቤት አንድ በር ብቻ ያለው ሲሆን ቀበሮዋ ያገኘችው ቤት ግን በከፊል የፈረሰና ብዙ ቀዳዳዎች ያሉት ነበር፡፡
ቀበሮዋም ጅቡን እንዲህ አለችው “ጠላት በዚህኛው ቀዳዳ ቢመጣብኝ በዚያኛው አመልጣለው፣ ሌላ ጠላት በዚያኛው ቀዳዳ በኩል ቢመጣብን በዚህኛው በኩል አመልጣለው፣ አንተ ግን ጠላት በበሩ በኩል ቢመጣብህ በየት በኩል ታመልጣለህ?”
ጅቡም “እሺ እንለዋወጥ፡፡ ቤቴንም ውሰጅና ያንቺን ቤት ልውሰድ::” አላት፡፡
በዚህም ሁኔታ ከተለዋወጡ በኋላ ቀበሮዋ ጅቡን እንዲህ አለችው “አሁን ውሃ ላመጣ ስለምሄድ ላሜ ልትወልድ ትችላለችና ጠብቅልኝ፡፡”
ጅቡም “እሺ” አለ፡፡
ቀበሮዋም ከቤት ወጥታ እንዳለች ላሚቷ በወለደች ግዜ ጅቡ እትብቱን ወስዶ በበሬው ፊንጢጣ ውስጥ አኖረው፡፡
ቀበሮዋም ከሄደችበት ስትመለስ እንዲህ ብላ ጠየቀችው “ላሜ ወለደች?”
ጅቡም “አይ ይህ የኔ ጥጃ ነው፡፡ የኔ በሬ ነው የወለደው::” አላት፡፡
እሷም “በሬ ይወልዳል እንዴ?” ብላ ብትጠይቀው እሱም “አዎ” አላት፡፡
እሷም “አይወልድም::” ብላ ተቃወመች፡፡
ከዚያም ወደ ዳኛ እንሂድ ብለው ተስማሙ፡፡ በመንገዳቸውም አንድ ዝንጀሮ አገኙ፡፡
ጅቡም ዝንጀሮውን “እዚህ ምን እየሰራህ ነው?” ብሎ ጠየቀው፡፡
ዝንጀሮውም “ውሃ እየቀዳሁ ነው::” ብሎ መለሰለት፡፡
በመቀጠልም ጅቡ “ውሃ ከድንጋይ ላይ ይቀዳል እንዴ?” ቢለው ዝንጀሮውም መለስ አድርጎ “ጥጃስ ከበሬ ይገኛል እንዴ?” ብሎ መለሰለትና በዚህ ሁኔታ ጅቡ ተሸነፈ፡፡
< ወደኋላ |
---|