ያባትየው ሃጢያቶች
በአህመድ መሃመድ አባት የተተረከ
ከእለታት አንድ ቀን ሰብሰብ ብለው ይሄዱ የነበሩ ወንዶች አንድ ከረጢት ስንዴና ሌሎች ጥራጥሬዎችን ይዘው ይጓዙ ነበር፡፡
አንዱ ሰውም እንዲህ አለ፡፡ “ከእናንተ ጋር መሄድ አልፈልግም፡፡ አንድ ፍሬ በቆሎ ስጡኝና ትቻችሁ ልሂድ፡፡”
ሌላኛውም “ምን ሆነሃል? ለምንድነው አብረን የማንሄደው? በቆሎውን ተካፍለን ምግባችንን በጋራ እያበሰልን እንካፈላለን፡፡ ነገር ግን አንድ ፍሬ በቆሎ ብትወስድ ምንም አያደርግልህም፡፡” አለው፡፡
ሰውየውም “ይህ አንተን አይመለከትህም፡፡ አንዷን ፍሬ በቆሎ ብቻ ነው የምፈልገው፡፡” ብሎ መለሰለት፡፡ ወጣቶቹም ሰዎች ተመካክረው እንዲህ ብለው ወሰኑ “አንድ ፍሬ በቆሎ ለእኛ ምንም ማለት አይደለም፡፡እንስጠው፡፡”
አንድ ፍሬ በቆሎውንም ሰጥተውት ሲሄድ በአንዲት ትንሽ መንደር ውስጥ የበቆሎ ምግም ታዘጋጅ የነበረች ሴት አግኝቶ አንዲቷን ፍሬ በቆሎ ማሰሮዋ ውስጥ ወርውሮ “ለእራት እመጣKG<፡፡” ብሎ ሄደ፡፡
እንግዳውን ሰው በመገረም ተመልክታው ዝም አለች፡፡ የዚያን እለት ምሽት የእራት ሰአት እስኪያልፍ ጠብቆ ወደቤቱ ተመለሰ፡፡ ሁሉም ሰዎች ምግባቸውን በልተው ጨርሰው ነበርና እንዲህ አሉት “ምግቡን ከጨረስን በኋላ በመምጣትህ እናዝናለን፡፡ ከእኛ ጋር ትመገብ ነበር፡፡”
እሱም አንዲት የበቆሎ ፍሬ ይዞ መምጣቱንና ነገር ግን ሴትየዋ በቆሎውን ስትፈጭ አንዲቷ ፍሬ የት እንደገባች አለማወቋን ነገራቸው፡፡ ከዚያም ጠንከርና በስጨት ብሎ “ወይ ምግቤን ስጡኝ አለበለዚያ ማሰሮውን ልውሰድ፡፡” አላቸው፡፡
እነእርሱም “እንዴት ያለው እብድ ሰው ገጠመን?” ብለው “እንግዲህ፣ ምግቡ ስላለቀ ምንም ልንሰጥህ አንችልም፡፡” አሉት፡፡ ከዚያም ተነጋግረው “አንድ ማሰሮ ለእኛ ምንም ማለት አይደለም፡፡” በማለት ማሰሮውን ሰጡት፡፡
ማሰሮውን ወስዶ ወደወንዝ በመውረድ ውሃ ከሞላ በኋላ ከመንገድ ዳር አስቀመጠው፡፡ ከዚያም የፍየሎች መንጋ ሲመጣ ተመልክቶ መንገዳቸው ላይ ማሰሮውን ስላስቀመጠው ፍየሎቹ ውሃውን መጠጣት ጀምረው አንገታቸውን ሊያስገቡበት ሲታገሉ ማሰሮውን ሰበሩት፡፡
በዚህ ግዜ የፍየሎቹን ባለቤት ጠርቶ “ተመልከት! ፍየሎችህ ማሰሮዬን ሰብረውብኛል፡፡ ወይ ማሰሮዬን ስጠኝ አለበለዚያ አንዲቷን ፍየል እወስዳለው፡፡” አለው፡፡
የፍየሎቹም ባለቤት “ችግር የለም፡፡ ሌላ ማሰሮ እሰጥሃለው” አለው፡፡ ሰውየው “የራሴን ማሰሮ እንጂ ሌላ አልፈልግም፡፡” አለ፡፡
የፍየሎቹም ባለቤት የተሰበረውን ማሰሮ መጠገን ስለማይችል ሳይወድ በግዱ አንድ ፍየል ሰጠው፡፡
ሰውየውም ፍየሏን ወስዶ በመሄድ ላይ እያለ ምሳቸውን በልተውና ጠግበው በመፈንጨት እየተመለሱ ያሉ ግመሎችን ሲመለከት ፍየሏን መንገዳቸው ላይ በማሰር ጨፈላልቀው እንዲገድሏት አደረገ፡፡
ከዚያም የግመሎቹን ጠባቂ አስቁሞ “ተመልከት ፍየሌን ገድለህብኛል፡፡ ወይ ፍየሏን ወደ ህይወት መልስልኝ አለበለዚያ አንድ ግመል ትሰጠኛለህ” አለው፡፡
እረኛውም “ይህ የማይቻል ነው፡፡ ፍየሏን እንዴት ነው ወደ ህይወት የምመልሳት? ሌላ ፍየል ፈልጌ እሰጥሃለው” አለው፡፡
ሰውየውም “አይሆንም ፍየሌን ወይንም ግመል” አለው፡፡
ፍየሏ ስለሞተች እረኛው አንድ ግመል ለመስጠጥ ተገደደ፡፡
ሰውየውም ግመሉን ይዞ በመሄድ ላይ ሳለ የጓደኛው የቀብር ስነ ስርአት ላይ ይደርሳል፡፡
“እስኪ አንድ ግዜ ቆዩኝ፡፡ የዚህን ሰው አስክሬን እፈልገዋለው፡፡ በግመል ለውጡኝ፡፡” አላቸው፡፡
ሰዎቹም ሰብሰብ ብለው አስክሬኑ ዋጋ እንደሌለውና ግመሉ እንደሚጠቅማቸው መክረው ሲያበቁ አስክሬኑን በግመል ለወጡት፡፡
ቀኑ እየመሸ ባለበት ሰአት ወደ አንዲት ትንሽ መንደር ሄዶ ሰዎች ተቀምጠው እየበሉ ያያቸውና “ጤና ይስጥልኝ፡፡ መንገደኞች ነን፡፡ ስለመሸብን ጓደኛዬን እዚህኛው ቤት፣ እኔ ደግሞ የሚቀጥለው ጎጆ ውስጥ እንደር፡፡” ብሎ ጠየቃቸው፡፡
ከዚያም አስክሬኑን ወንበር ላይ አስቀመጠው፡፡ ሰዎቹም የሞተ ሰው አልመሰላቸውም፡፡ ወደ ውጪ በመውጣት ላይ እያለ አስክሬኑን በጦር ወግቶት ወደ አጎራባቹ ቤት ሄደ፡፡ በአፋር ባህል መሰረት ምግብ የሚፈልግ ሰው እንደ እንግዳ ስለሚጋበዝ እራቱን ሰጡት፡፡ እራቱን እየበላ ሳለም ከሚቀጥለው ጎጆ የጩኸት ድምፅ ሰማ፡፡ “ጓደኛዬን እዚያ ነው የተውኩት፡፡ ሄደን እንየው፡፡” አላቸው፡፡ ወደሚቀጥለው ጎጆም እየሮጡ ሲሄዱ አጎራባች ያሉት ሰዎች አስክሬኑ በጦር ተወግቶ አገኙት፡፡
በዚህ ግዜ ጓደኛዬን ገደሉብኝ እያለ መጮህ ጀመረ፡፡ ብጥብጥና ጩህትም ስለበረከተ ጎረቤቶቹ ጓደኛውን እንደገደሉበት ተወሰነ፡፡ በዚህም ካሣ ሊሰጠው ይገባል፡፡ የአንድ ሰው ካሣ ደግሞ 100 ግመሎች ወይም 400 ከብቶች ነው፡፡ ሰውየውም ግማሹን በግመሎችና ግማሹን ደግሞ በከብቶች ተከፍሎት ሃብታም ሰው ሆነ፡፡
ሁለት ሚስቶችንም አግብቶ ከአንደኛዋ አራት ልጆችን ከሁለተኛዋ ሚስቱ ደግሞ አንድ ወንድ ልጅ ብቻ ወለደ፡፡ ከዚያም ለብዙ አመታት በደስታ ኖሮ ሞተ፡፡ ሲሞት አስክሬኑ በግመል ጀርባ ላይ ተጭኖ ወደ መቃብር ቦታው እንዲወሰድ ተናዞ ስለነበር በግመል ጭነው እየወሰዱት ሣለ ግመሉ ደንብሮ መሮጥ ስለጀመረ ግራ ገባቸው፡፡ በጣም ሃብታምና ታዋቂ ሰው ስለነበር ሰው ሁሉ የአስክሬኑን መምጣት በጉጉት ይጠብቅ ነበር፡፡ በተጨማሪም ልጆቹ አስክሬኑ ካልተቀበረ በውርስ ላይ ችግር እንደሚገጥማቸው ያውቃሉ፡፡
ከዚያም አራቱ የመጀመሪያዋ ሚስት ልጆች እንዲህ ብለው አሰቡ “ወንድማችንን ለምን አንገድለውም? ከዚያም የሚቀበር አስክሬን ስለሚኖረንና ሁሉም ነገር የእኛ ብቻ ስለሚሆን በውርስ ላይ ችግር አይኖርብንም፡፡”
ስለዚህ ወንድማቸውን ገድለው ወደ መቃብር ቦታው ወስደው በመቅበር ላይ ሳሉ የአባታቸውን አስክሬን ይዞ የጠፋው ግመል አስክሬኑን ይዞ ተመልሶ መጣ፡፡
ነገር ግን የአባትየው አስክሬን ሙሉ ለሙሉ ተበጣጥሶ ስላለቀ ግመሉ ጀርባ ላይ የቀረው ጭንቅላቱ ብቻ ነበር፡፡ ሰዎቹም ግመሉን አቁመው ሲመለከቱ እየቀበሩ ያሉት የመሰላቸውን ሰው ጭንቅላት ተመለከቱ፡፡ እናም እንዲህ አሉ “ለምን? ይህ እየቀበርነው ያለው ሰው ጭንቅላት አይደለም?”
ከዚያም አስክሬኑን ፈተው ሲመለከቱ የልጁ አስክሬን መሆኑን ደረሱበት፡፡ በዚህም ምክንያት የመጀመሪያዋ ሚስት ቤተሰቦች በሙሉ ከሁለተኛዋ ሚስት ቤተሰብ ጋር ጦርነት ከፍተው እርስ በእርስ ተጨራረሱ፡፡
ይህ ተረት የሚያመለክተው አንድ ሰው በሌሎች ላይ ክፉ በሰራ ቁጥር ለጊዜው ስኬት ቢገጥመውም ሃጢአቱ ለልጆቹ እንደሚተላለፍ ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|