የፆታ ለውጡ
በአሎ ያዮ ባሩሌ የተተረከ
በአፋር ባህል ወንድ በጣም የተከበረ ቢሆንም አማቱን ይፈራል፡፡ ከእለታት አንድ ቀን ታዲያ ባልና ሚስት አብረው ሲኖሩ ሚስትየው ውሽማ ነበራት፡፡ ሚስትየዋም አንድ ቀን ውሽማዋን ወደቤት ልታመጣው ወስና ለባሏ እናቷ ልትጎበኛቸው እንደምትመጣና ለአንድ ሳምንት ለሚቆይ ድግስ ዝግጅቱ በሙሉ መጠናቀቁን ትነግረዋለች፡፡ ለውሽማዋ ደግሞ ባሏ እንዳያየው ማታ እንዲመጣና እናቷ ስለምታዘወትራቸው ጌጣጌጦች፣ ልብሶችና ጫማዎች ነግራው ስታበቃ ውሽማው የሚስተየዋን እናት አለባበስ ለብሶ ይመጣል፡፡ ሰው አክባሪውም የልጅ ባል ከሩቅ አጎንብሶ እጅ ከነሳ በኋላ ከጎጆው ወጥቶ ማደር ጀመረ፡፡ በዚህም አይነት ሰው አክባሪው የልጅ ባል ውጪ እያደረ ለረጅም ግዜ ቆዩ፡፡ አንድ ቀን ታዲያ የልጅ ባል ከሚያድርባት ጎጆ ሲሄድ ሚስትየውም ማገዶ ልታመጣ ትሄዳለች፡፡¨ባልየውም በመንገዱ ላይ አንድ ትልቅ ዛፍ አይቶ መቁረጥ ስለፈለገ መጥረቢያ ሊያመጣ ወደጎጆው ይመለሳል፡፡ ታዲያ ባልየው ከሩቅ ቢጣራም ሚስትየው እቤት ስላልነበረችና ውሽማዋም ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ስለነበረ ማንም መልስ የሚሰጠው ሰው ያጣል፡፡ ስለዚህ ወደ ቤቱ ውስጥ ዘልቆ አልጋው ስር የነበረውን መጥረቢያ ይዞ ሊወጣ ይወስናል፡፡ የቤቱ መስኮት ክፍት ስለነበር አማቱ ተኝተው እንደነበረ ያያል፡፡ ወደ ቤቱ ውስጥም ዘልቆ መጥረቢያውን ካልጋው ስር እያወጣ ሳለ ቀና ሲል አንድ ያልተለመደ ነገር ያያል፡፡ያየውም እንግዳ ነገር ከአማቱ ቀሚስ ስር የሆነ የቆመ ነገር ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ በባህሉ መሰረት ቀሚሳቸውን ከፍ አድርጎ የቆመውን ነገር በመያዝ በገጀራ ቀንጥሶ ይጥለዋል፡፡ ከዚያም በግራ እጁ የቆረጠውን ነገር አንጠልጥሎ በቀኝ እጁ ደግሞ በደም የተነከረውን ገጀራ በመያዝ የሚስቱን አንገት ለመቁረጥ ፍለጋ ይሄዳል፡፡
ሚስትየውም ባሏ የውሽማዋን ብልት በግራ እጁ ገጀራውን በቀኝ እጁ ይዞ ወደእሷ እየመጣ ባየች ግዜ “ይሄ እርግማን ነው፣ እርግማን ነው”! እያለች መጮህ ጀመረች:: ባልየውም በመገረም እየተከታተላት በመሮጥ “ምን ሆነሻል? ለምንድነው የምትጮሂው?” ብሎ ጠየቃት፡፡
እሷም “አታምነኝም፣ የእናቴ ቤተሰቦች ከአንድ ጠንቋይ ጋር ትልቅ ፀብ ስለነበራቸው ጠንቋዩ ሴቶቹን ወደ ወንድነት ወንዶቹን ሁሉ ደግሞ ወደ ሴትነት ቀየራቸው፡፡ ይህ በጣም መጥፎ አጋጣሚ ነው::” አለችው፡፡ ባልየውም እንዲህ ሲል መለሰ “ትክክል ነሽ፡፡ እናትሽም ወደ ወንድነት ተለውጣ ነበር፡፡ አሁን አትጨነቂ፡፡ አንቺ እስካልተለወጥሽ ድረስ ችግር የለም፡፡”
ከዚያም ወደቤታቸው ተመልሰው በደስታ አብረው መኖር ጀመሩ፡፡
ይህ የሚያሳየው ብልህ ሴት ባሏን እንደፈለገችው አድርጋ መያዝ እንደምትችል ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|