መስማት የተሳነው ቤተሰብ
በመሃመድ አህመድ የተተረከ
በአንድ ወቅት በአንድ ስፍራ የሚኖር ቤተሰብ ነበር፡፡ በቤተሰቡ ውስጥ አንድ አባወራና ባለቤቱ ከሴት ልጃቸው ጋር ይኖሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ሶስቱም መስማት የተሳናቸው ነበሩ፡፡ ከእለታት አንድ ቀን አመሻሽ ላይ አባወራው አህያውን ወደ ወንዝ ወስዶ ውሃ ሊያጠጣው ፈልጎ አህያውን እየነዳ ወደ ወንዝ ወረደ፡፡ ወንዙ አጠገብ እንደደረሰም ሌሎች ብዙ እረኞች ከብቶቻቸውን ውሃ ያጠጡ ነበር፡፡ እነእርሱም “ሰማህ አንተ ሰው? ከብቶቻችን እየጠጡ ነው፡፡ ያንተ ግን አህያ ስለሆነ ከብቶቻችን ቀድመው ይጠጡ፡፡” አሉት፡፡
መስማት የተሳነውም ሰው “ይቅርታ አህያዬ የሚሸጥ አይደለም፡፡” አላቸው፡፡
እነርሱም “ሰውየው ምን ነካው?” ብለው አሰቡ፡፡ እንዲህም አሉት “ያንተ አህያ ቢሸጥ ባይሸጥ ግድ የለንም፡፡ ከከብቶቻችን ቀድሞ እንዳይጠጣ ነው የምንፈልገው፡፡”
ሰውየውም ቀና ብሎ አይቷቸው “የምናገረውን አትሰሙም እንዴ? አህያዬ አይሸጥም አልኳችሁ እኮ፡፡” አላቸው፡፡
እረኞቹም “ሰውየው እብድ ነው?” ብለው አስበው ዝም አሉት፡፡
አህያውም ውሃውን ጠጥቶ ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡
ሰውየው ወደቤት እንደደረሰም ወደ ኩሽና ሄዶ ሚስቱን እንዲህ አላት “ይገርምሻል! ዛሬ ነጋዴዎችን መንገድ ላይ አግኝቼ ‘አህያህን ካልሼጥክልን’ ብለው ሲያስቸግሩኝ የሚሸጥ አንዳልሆነ ነገርኳቸው፡፡” ሚስቱም ቀና ብላ አይታው Uንም ሳትሰማው እንዲህ አለችው “እንግዲያውማ ልትፈታኝ ከወሰንክ አንድም ቀን ካንተ ጋር ማደር ስለማልፈልግ ወደ ቤተሰቦቼ እሄዳለG<፡፡”
ትታውም ልትሄድ እቃዎቿን እየሰበሰበች እያለች ልጃቸው ወደ ቤት ስትገባ ሚስትየው ቀና ብላ አይታት “ይገርምሻል! ከእነዚያ ብዙ የትዳር አመታት በኋላ አባትሽ ሂጂልኝ አለኝ እኮ” አለቻት፡፡
ልጅቷም የሃፍረት ፈገግታ አሳይታ ቀና ብላ እንግዲህ “እናንተ ወላጆቼ ናችሁ፡፡ ልትድሩኝ ከፈለጋችሁ በሃሳባችሁ እስማማለG<፡፡” አለቻቸው ይባላል፡፡
የዚህ ተረት መልዕክትም ሰው የሚሰማው መስማት የሚፈልገውን ነገር ብቻ እንደሆነ ያሳየናል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|