ብልጡ ልጅ
ተራኪው የማይታወቅ
በአንድ ወቅት በጣም ብልጥ የሆነ የ15 ዓመት እድሜ ያለው የአፋር ተወላጅ ልጅ ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ልጅ በቤቱ ውስጥ ይደረግ የነበረውን መጥፎ ነገር ያውቅ ስለነበረ ሁልጊዜ ያዝንና ይበሳጭ ነበር፡፡ አባቱ ከእናቱ ገረዶች ከአንድዋ ጋር በድብቅ ይባልግ ነበር፡፡ እናቱም ከቤሰተቡ ውጪ ከአንድ ሰው ጋር ትማግጥ ነበር፡፡ ልጁም ይህንን ሁሉ ስለሚያውቅ በጣም ይናደድ ነበር፡፡ እናም ከእለታት አንድ ቀን በቤቱ ውስጥ አንድ ጥግ ላይ ተሸፋፋኖ ተኝቶ ሳለ የእናቱ ወዳጅ ወደ ውስጥ ሲዘልቅ ልጁን አላስተዋለውም፡፡
እናም እናቱን እንዲህ አላት “አንቺ በጣም ደግ ሴት ነሽ፡፡ የጠየኩሽን ሁሉ ሰጥተሽኛል፡፡ አሁን ደግሞ የባለቤትሽን ትልቅ ነጭ በሬ በነገው እለት መብላት እፈልጋለሁ፡፡” አላት፡፡ የልጁም እናት “ምንም ችግር የለም፤ አንተ ብቻ አስር የሚሆኑ ጓደኞችህን ይዘህ መምጣት አለብህ፡፡” አለችው፡፡
በማግስቱም ወዳጅዋ አስር ጓደኞቹን አስከትሎ መጣ፡፡ እስዋም ወደ ባሏ ሄዳ እንዲህ አለችው “ይኸውልህ ዘመዶቼ በሙሉ ስለመጡ ልንመግባቸው ይገባል፣ ቁጥራቸውም በጣም ብዙ ስለሆነ እንጀራና እንጀራ በኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች ከሚበቅለው ጤፍ የተባለ ሰብል የሚሰራ ጠፍጣፋ፣ ስስና ክብ ምግብ ነው፡፡ ሌላ ተራ ምግቦችን ማቅረብ አልፈልግም፡፡”
ባልየውም እንዲህ አላት “እንግዲያው ትልቁን ነጭ በሬዬን አርደን እናበላቸዋለን፡፡”
እናም ባልየው ትልቁን በሬ ከአንድ ዛፍ ስር ወስዶ በትልቅ ቢላዋ ያርደው ጀመር፡፡ ልጁም በጣም ተበሳጭቶ ሳለ ወደ አባቱ ዘንድ ሲሄድ አባትየው የበሬውን ስጋ ቆራርጦ ጨርሶ ልጁን ስጋውን ለእንግዶች እንዲያደርስ ያዘዋል፡፡ ልጁም ስጋውን ይዞ ወደ ቤት በመመለስ ላይ ሳለ በመንገዱ ላይ ባገኛቸው ድንጋዮች በእያንዳንዳቸው ላይ አንድ የስጋ ቁራጭ እያስቀመጠ ያልፍ ጀመር፡፡ ይህንንም እያደረገ እንግዶቹ ድረስ ዘለቀ፡፡ አባትየውም የስጋውን ቁራጭ በየድንጋዩ ላይ ባየ ጊዜ “ልጄ ምን ነካው?” ብሎ አሰበ፡፡
በአንድ እጁ ቢላዋውን እንደያዘ በሌላኛው እጁ ጎንበስ እያለ የስጋውን ቁራጮች እየሰበሰበ ልጁን ይከተለው ጀመር፡፡
ልጁ ወደ እንግዶቹ እየሮጠ በሄደ ጊዜ የእናቱ ወዳጅ እንዲህ ብሎ ጠየቀው “አባትህ ምን እያደረገ ነው?”
ልጁም “አትመለከትም? ሳንጃውን ወድሮና ድንጋይ እየለቀመ ወደ እኛ እየመጣ ነው፡፡ ከእናቴ ጋር ያለህን ድብቅ ወዳጅነት ስለደረሰበት ሊገድልህ እየመጣ ነው፡፡” አለው፡፡
ሰውየውና እንግዶቹም ተነስተው መሮጥ ጀመሩ፡፡ አባትየውም ተከትሎ ሊያስቆማቸው ሞከረ፡፡
በዚህ ጊዜ ልጁ ወደ እናቱ ሲሄድ እናቱ “ይህ ሁሉ ብጥብጥ ምንድነው?” ብላ ጠየቀችው፡፡
ልጁም እንዲህ ሲል መለሰ “አባቴ ያንቺንና የወዳጅሽን ድብቅ ፍቅር ስለደረሰበት ወዳጅሽን በድንጋይ ሊደበድበው እያሳደደው ነው፡፡ ከዚያም ወደ ቤት ተመልሶ ጉሮሮሽን ይቆርጠዋል፡፡”
በዚህ ጊዜ እናትየው በጣም ደንግጣ ወደ እናትዋ ቤት መሮጥ ጀመረች፡፡
አባትየውም እንግዶቹ ላይ እንደማይደርስባቸው ባወቀ ጊዜ ልጁን ጠርቶ “ምን እየተካሄደ ነው?” ብሎ ጠየቀው፡፡
ልጁም “እናቴ ያንተንና የገረድዋን ድብቅ ፍቅር ስለደረሰችበት ለእናትዋ ልትነግር እየሮጠች ነው፡፡” ይለዋል፡፡
አባትየውም ከኋላ ከኋላዋ እየሮጠ “እባክሽ፣ እባክሽ በፈጣሪ ስም ለእናትሽ አንዳችም ነገር እንዳትነግሪያት” እያለ ይማፀናት ጀመር፡፡
ሚስቱም እየተከተላት መሆኑን ስታውቅ ሩጫዋን ቀጠለች፡፡ “እባክህ አትግደለኝ፣ ጉሮሮዬንም አትቁረጠው” እያለች ትለምነው ጀመር፡፡ ልጁም ተከትሏቸው ይሮጥ ነበር፡፡ ሁለቱም ከሚስትየው እናት ቤት እኩል ደረሱ፡፡ እናትየውም ሚስትየዋን ተመልክተው “ምን ሆነሻል?” ብለው ጠየቋት፡፡
እሷም “ልነግርሽ አልችልም፡፡ ልነግርሽ አልችልም፣ ምክንያቱም ልጄ ያውቀዋል፡፡” አለቻቸው፡፡
እናትየው ወደ አማቻቸው ዞር ብለው “አንተስ ምን ሆነሃል?” ብለው ጠየቁት፡፡
እሱም “እኔም ልነግሮዎት አልችልም፡፡ ምክንያቱን የሚያውቀው ልጄ ብቻ ነው፡፡” አላቸው፡፡
በዚህ ጊዜ ልጁ ይደርስና “ችግር የለውም፤ ወደቤታችን እንመለስና ችግሩን እኔ እፈታዋለሁ፡፡” አላቸው፡፡ ከቤት እንደደረሱም ልጁ ሁለቱን ለየብቻ እየጠራ በማነጋገር አባትየውን “ከዚህ በኋላ ድርጊትህን የምታቆም ከሆነ እናቴ ልትምርህ ፈቃደኛ ነች፡፡” አለው፡፡ ከዚያም ወደ እናትየው ሄዶ “ከዚህ በኋላ ድርጊትሽን የምታቆሚ ከሆነ አባቴ ሊምርሽ ፈቃደኛ ነው፡፡” አላት፡፡
በዚህ ሁኔታ ሁለቱም አንዱ የሌላውን ያለመታመን ምስጢር ሳያውቅ በደስታ መኖር ጀመሩ፡፡ ይህ ታሪክ ብልህ ልጅ የቤተሰቡ ኩራት መሆን እንደሚችል ያሳያል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|