አራቱ ወንድማማቾችና አያ ጅቦ
ተራኪው የማይታወቅ
በአንድ ወቅት አራት ወንድማማቾችና ከመንደራቸው አካባቢ የሚገኝ ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ነበር፡፡ ይህ ጫካ ተደፍሮ የማያውቀው በጅቦች ንጉስ ስለሚተዳደር በመሆኑና በደኑ ውስጥ በጣም ብዙ አስፈሪ ጅቦች ስለሚዘዋወሩበት አንድም ሰው ድርሽ ስለማይልበት ነበር፡፡
ታዲያ ከእለታት አንድ ቀን አራቱ ወንድማማቾች ወደ ጫካው ዘልቀው በመግባትና ውስጡን ለመመልከት ወስነው ወደዚያው አቀኑ፡፡ ወደ ጫካው እንደዘለቁም መጀመሪያ ምንም አላጋጠማቸውም፡፡ ሆኖም ወደ ጫካው መሃል በደረሱ ጊዜ በብዙ የጅቦች ሰራዊትና በንጉሳቸው መከበባቸውን አስተዋሉ፡፡
የጅቦቹም ንጉስ ጠርቷቸው “እንዴት ብትዳፈሩ ነው ወደ ደኔ ውስጥ የገባችሁት? ወደ እኔ ንጉሳዊ ግዛት ውስጥ ደፍራችሁ እንድትገቡ ያበረታታችሁን ምክንያት ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡” አላቸው፡፡
የመጀመሪያውንም ወንድም ጠርቶ “አንተ በማን ተማምነህ ነው?” ብሎ ቢጠይቀው እሱም “መመኪያዬ አምላኬ ነው፤ የዚህ ሁሉ አለም ፈጣሪ እንደፈጠረኝ ሁሉ የህይወቴ ትልምና የምሞትበትም ቀን ጭምር በመፅሃፉ ውስጥ ተፅፈው ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ምንም የሚያስፈራኝ ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ቀድሞ ተወስኖልኛልና፡፡” ብሎ መለሰለት፡፡
የጅቦቹም ንጉስ ወደ ሁለተኛው ወንድም ዞሮ “አንተስ መመኪያህ ማነው?” አለው፡፡ ሁለተኛውም ወንድም “የኔ መመኪያ የጎሳዬ አባላት ናቸው፡፡ እነርሱም በጣም ደፋርና ቁጡ ስለሆኑ ከቤተሰባቸው አንድም ሰው በከንቱ እንዲሞት አይፈቅዱም፡፡ ስለዚህ ማንም እኔን ቢገድል የጎሳዬ አባላት ሄደው ይበቀሉታል፡፡ ስለዚህ ማንንም አልፈራም፡፡” አለው፡፡
የጅቦቹ ንጉስ ወደ ሶስተኛው ዞሮ “አንተስ? በምንድነው የምትመካው?” ብሎ ጠየቀው፡፡
ሶስተኛውም ወንድም “እኔ የምመካው የሁላችንም እናት በሆነችውና እኔንም በፈጠረችኝ በምድራችን ነው፡፡ የመሞቻዬም ቀን በደረሰ ጊዜ ሞቼ የምቀበረው በእርሷ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ እምነቴን ሁሉ በምድር ላይ ጥየዋለሁ፡፡” ብሎ መለሰለት፡፡
በመጨረሻም ንጉሱ አራተኛውን ወንድም “አንተስ?” ብሎ ቢጠይቀው አራተኛው ወንድም “የእኔ መመኪያ እናንተ ጅቦች ናችሁ፡፡ አያችሁ፣ ጥቂት የጅብ ጓደኞች አሉኝ፡፡ እነርሱም በጣም ጠንካራ ጎበዞች ስለሆኑ በእናንተው በጅቦች ነው የምተማመነው” ሲል መለሰለት፡፡
ንጉሱም ወታደሮቹን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፡፡ “ተመልከቱ፣ የመጀመሪው ሰው በፈጣሪ ነው የሚተማመነውና እኛም ከፈጣሪ ጋር መጣላት አንችልም፡፡ ስለዚህ በነጻ እንለቀዋለን፡፡ ሁለተኛው ሰው የሚመካው በጎሳዎቹ አባላት ስለሆነ ከጎሳ ጋር መጣላት እንደማንችል ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ እርሱም በሰላም ይሂድ፡፡ ሶስተኛውም ሰው በእናት ምድራችን የሚመካ በመሆኑ በላይዋ ላይ እየኖረ ከምድር ጋር ማን ይጋጫል? ስለዚህ እርሱም በሰላም ይሂድ፡፡ ነገር ግን አራተኛው ሰው የሚተማመነው በእኛው በጅቦች ነው፡፡ እኛም እርስ በእርስ ብንጣላ ምንም ችግር የለውምና በሉ እርሱን እንብላው፡፡” ብሎ አራተኛውን ወንድም በሉት ይባላል፡፡
ወደሚቀጥለው > |
---|