ሞት አነሰው
ተራኪው የማይታወቅ
በአንድ ወቅት ነብር መግደል የፈለጉ ሁለት ሰዎች ነበሩ፡፡ ነብሩም አይቷቸው ሲሮጥ በመንገዱ ላይ አንድ ገበሬ አገኘ፡፡
ገበሬውም እርሻውን እያረሰ እንዲህ እያለ ይዘፍን ነበር፤
“እኔ እያረስኩ ነው
ደመናዎቹን እያየሁ
ዝናብ የሚያመጡልኝን፡፡”
ነብሩም “የዘሩን ከረጢት አቀብለኝና ከአዳኞቹ አድነኝ እባክህ፡፡” ብሎ ገበሬውን ጠየቀው፡፡
ገበሬውም እሺ ብሎ ነብሩን የዘር መያዣው ውስጥ ደበቀው፡፡ ሁለቱም አዳኞች ገበሬው ጋ ሲደርሱ ቆም ብለው “አንድ ነብር አይተሃል” አሉት፡፡
ገበሬውም “አዎ በዚህ በኩል ሄዷል፡፡” አላቸው፡፡ አዳኞቹም ሩጫቸውን ቀጠሉ፡፡
በዚህ ጊዜ ገበሬው ነብሩን “ነብር ሆይ አዳኞቹ ስለሄዱ በል ሂድ፡፡” አለው፡፡
ነብሩ ግን “ወይ እገድልሃለሁ ወይም ምግብ አምጣልኝ፡፡” አለው፡፡
ገበሬውም “ለምን ስላዳንኩህ ነው የምትገድለኝ?” ብሎት “በል አህያዋ ጋ ሄደን ትዳኘን፡፡” አለው፡፡
አህያዋ ጋም ሄደው ገበሬው “እኔ ነኝ መበላት ያለብኝ?” ሲላት አህያዋም “አዎን፣ ለምን አትበላም?” አለችው፡፡
ከዚያም ወደ ቀበሮ ሄዶ ገበሬው “ይህንን ነብር ከሞት አዳንኩት፤ ሆኖም አሁን ሊበላኝ ይፈልጋል፡፡” አላት፡፡
ቀበሮዋም “እንዴት ነው የዳንከው” ስትለው ስለአዳኞቹና ነብሩ ስለተደበቀበት የዘር ክምር ነገራት፡፡
ከዚያም ቀበሮዋ “በል እንዴት እንደነበረ አሳየኝ፡፡” ስትለው ገበሬው ነብሩን እንደገና ደበቀው፡፡
በዚህ ጊዜ ቀበሮዋ ገበሬውን “በል አሁን አጥብቀህ እሰረው፡፡” ስትለው ገበሬው ነብሩን ጥፍር አድርጎ ካሰረው በኋላ ቀበሮዋ “በል አሁን ደግሞ ደብድበው፡፡” አለችው፡፡
ገበሬውም ነብሩን ደብድቦ ገደለው፡፡
ከዚያም ገበሬው ቀበሮዋን “ከሞት አድነሽኛልና ምን ላድርግልሽ?” አላት፡፡
እርሷም “አንድ ጥሩ በግ አምጣልኝ፡፡” አለችው፡፡
ገበሬው ግን አንድ ትልቅ ውሻ ሲያመጣ ቀበሮዋ አይታ “ለሰው ሞት አነሳው፡፡” አለች ይባላል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|