የቄሱ ሚስትና ውሽማዋ
ተራኪው የማይታወቅ
ቄሱ ወደ ቤተክርስቲያን በሄዱ ጊዜ ውሽማው በድብቅ እየመጣ ከሚስታቸው ጋር ይተኛ ነበር፡፡
ከእለታት አንድ ቀን ታዲያ ሴትየዋ ውሽማዋን በጣም አፍቅራው ነበርና በጠዋት ተነስታ ቄሱን “ሰአትዎ ደርሶቦታልና ወደ ቤተክርስቲያን አይሄዱም እንዴ?” አለቻቸው፡፡
ቄሱም ተነስተው ሲወጡ ውሽማው መጥቶ እርሷ ገንፎ ስትሰራ ቄሱ በመንገዳቸው ጅብና ሌሎች አውሬዎች ስላጋጠሟቸው ገና እንዳልነጋና ከሌሊቱ ወደ አስር ሰአት ገደማ መሆኑን ስላወቁ ወደቤታቸው ተመለሱ፡፡
ሚስታቸውም የቄሱን መመለስ ስታውቅ ውሽማዋ አልጋው ስር እንዲደበቅ ነግራው ገንፎ መስራቷን ቀጠለች፡፡
ቄሱም “በዚህ ሰአት ለምንድነው ገንፎ የምትሰሪው?” ሲሏት እርሷም “ሰአት ሳይደርስ ስለቀሰቀስኮት መመለስዎን አውቄ ለእርስዎ ነው የምሰራው፡፡” አለቻቸው፡፡
እናም ቄሱ አልጋ ላይ ሲቀመጡ ገንፎውን ሰጥታቸው እርሷ መሬት ላይ ተቀመጠች፡፡ አብረውም መብላት ጀመሩ፡፡ ቄሱም ፊታቸውን ዞር ሲያደርጉ እርሷ ገንፎውን ለውሽማዋ ትሰጠዋለች፡፡ ታዲያ በድንገት አፉን ስታ ትኩሱን ገንፎ ፊቱ ላይ ስታደርግበት በጣም ስላቃጠለው ብድግ ሲል አልጋውና ቄሱ ተገለበጡ፡፡
ቄሱም በጣም ሲደነግጡ ሴትየዋ “ከሰይጣን ጋር ነው የመጡትና “እግዜር ማረኝ፣ እግዜር ማረኝ” ይበሉ ብላ ፀበል ፊታቸው ላይ ስትረጭባቸው ውሽማው ማንነቱ ሳይታወቅ ሮጦ አመለጠ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|