ቀበሮ፣ አባ ኮዳና፣ ጥንብ አንሳ
ተራኪው የማይታወቅ
አባ ኮዳዋ ዛፍ ላይ ጫጩቶች ፈልፍላ ቀበሮው ይህንን ሲያውቅ “አንቺ አባ ኮዳ! ከጫጩቶችሽ አንዷን ካልሰጠሽኝ ዛፉን ቆርጬው ሁላችሁንም ነው የምበላችሁ፡፡” አላት፡፡
እናም አባ ኮዳዋ አንዲት ጫጩት ሰጠችው፡፡ እንደዚያ እያሉ አንድ በአንድ ጫጩቶቹ መሄድ ጀመሩ፡፡ ጥንብ አንሳውም በመጣ ጊዜ የጫጩቶቹ ቁጥር እየቀነሰ ሄዶ ጥቂት ብቻ መቅረታቸውን አየ፡፡
እርሱም አባ ኮዳዋን ጫጩቶቹ ለምን እንደቀነሱ ሲጠይቃት እርሷም ስለቀበሮው ነገረችው፡፡
ጥንብ አንሳውም “ቀበሮ መጥረቢያ ስለሌለው ዛፍ መቁረጥ አይችልም፡፡” አላት፡፡
እሷም “እንደዚያ ነው?” አለች፡፡
ቀበሮውም ተመልሶ ሲመጣ አባ ኮዳዋ “በል ዛፉን ቁረጠው፡፡” አለችው፡፡
ቀበሮውም “ይህን የነገረሽ ጥንብ አንሳው መሆን አለበት፡፡” አለ፡፡
ከዚያም ቀበሮው ተመልሶ ሄዶ የአህያ አንጀት በመልበስ ጎዳና ላይ ሲቀመጥ ጥንብ አንሳው ስጋ አገኘሁ ብሎ ቀበሮው ላይ ቁጭ ሲል ቀበሮው ያዘው፡፡
ጥንብ አንሳውም “እባክህ የጥራጥሬ በርሜል ውስጥ አትወርውረኝ እንጂ የፈለከውን ልታደርገኝ ትችላለህ፡፡” አለው፡፡
በዚህ ጊዜ ቀበሮው ጥንብ አንሳውን የጥራጥሬ በርሜል ውስጥ ሲከተው ጥራጥሬውን በሙሉ በልቶ ስለጠገበ እንቅልፍ ወሰደው፡፡ ቀበሮውም ተመልሶ ሲመጣ ጥንብ አንሳው የሞተ መስሎት ሲይዘው ጥንብ አንሳው “እባክህ፣ የፈለከውን ነገር አድርግ፤ ነገር ግን ከነበርሜሉ ወደ ጫካ እንዳትወረውረኝ፡፡” አለው፡፡ ቀበሮው ጥንብ አንሳውን ከነበርሜሉ ወደ ጫካ ሲወረውረው በርሜሉ እየተንከባለለ ሲሄድ ቀበሮው ጥንብ አንሳውን እይዛለሁ ብሎ አብሮ ሲሮጥ በርሜሎ ጨፍልቆ ገደለው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|