ጅብ፣ ቀበሮና ጦጣ
ተራኪው የማይታወቅ
በአንድ ወቅት ጅብ፣ ቀበሮና ጦጣ በአንድ ቤት ውስጥ ይኖሩ ነበር፡፡ ከእለታት አንድ ቀን አደን ተሰማርተው በመንደሩ የሚኖር ገበሬ ንብረት የነበሩ አራት ላሞችን ሰረቁ፡፡
ከዚያም ጅቡ “እያንዳንዳችን አንድ ላም ይደርሰናል፡፡ ነገር ግን አራተኛዋን ላም ማነው የሚወስዳት?” አለ፡፡
ቀበሮውም “በእድሜ ከሁላችንም አንጋፋ የሆነው ይወስዳታል፡፡” አለ፡፡
ጦጣውና ጅቡም በዚህ ተስማሙ፡፡
ከዚያ በኋላ ቀበሮው ጅቡን “መች ነው የተወለድከው?” አለው፡፡ ጅቡም “አምና አይደለም፤ ካቻምናም አይደለም፡፡ ከብዙ አመታት በፊት ነው፡፡” ብሎ መለሰ፡፡
ቀበሮው ጦጣውንም “አንተስ መች ነው የተወለድከው? ብሎ ሲጠይቀው ጦጣው “እኔማ በመጀመሪያው ቀን ነው የተወለድኩት፡፡ ጌታ ምድርንና ሰማይን ሲፈጥር ነው የተወለድኩት፡፡” አለ፡፡
ቀበሮውም “ትክክል ነህ፡፡ በደንብ ነው የማስታውሰው፣ አንተ በተወለድክ በሰባተኛው ቀን ድግስ ተጥሎ ነበር፡፡ እኔም የክብር እንግዳ ነበርኩ፡፡” ሲል ጅቡና ጦጣው “እንግዲያውማ የሁላችንም ታላቅ አንተ ነህ፡፡” ብለው አራተኛዋን ላም ሰጡት፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|