ኪናማ
በአበበ ከበደ የተተረከ
ኪናማ ብዙ ፍየሎች የነበሯት የሲዳማ እረኛ ልጃገረድ ነበረች፡፡ ኪናማ ትኖር የነበረው በአንድ በጣም ግዙፍ የአለት መዝግያ በነበረው ትልቅ ዋሻ ውስጥ ነበር፡፡
ፍየሎቿን ወደ ግጦሽ ይዛ ስትሄድ ሁለት ከባድ ችግሮች ነበሩባት፡፡ አንደኛው ሁልግዜ ልጆቿን እየሰረቀ የሚያስቸግራት ነብር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሁልጊዜ የሚያስቸግራት ጅብ ነበር፡፡ ነገር ግን ዋነኛው ጠላቷ ነብሩ ስለነበረ ሁልጊዜ ልታሞኘው ትሞክር ነበር፡፡ ጠዋት ትነሳና ፍየሎቿን ከዋሻ ውስጥ “ግዙፉ ዋሻዬ ሆይ! በርህን ክፈተው!” እያለች የዋሻው መዝጊያ አለት ሲከፈት ልጆቿን ይዛ ትወጣለች፡፡
ከዚያም በግሩም ድምጿ ጮክ ብላ “ዛሬ ፍየሎቼን ወደ ዲጋሬ ይዣቸው እሄዳለሁ፡፡” ብላ ትናገራለች፡፡
ሆኖም ወደ ዲጋሬ ሳይሆን ወደ ተመዴ ትሄዳለች፡፡ በሌላ ቀን ደግሞ ጠዋት ትነሳና “ዛሬ ወደ ተመዴ ነው የምሄደው፡፡” ብላ ተናግራ ወደ ዲጋሬ ትሄዳለች፡፡
እናም በየቀኑ በዚህ ዓይነት ነብሩን እያታለለች “ግዙፉ ዋሻዬ ሆይ! በርህን ክፈት፡፡ ግዙፉ ዋሻዬ ሆይ! በርህን ዝጋ፡፡” እያለች ትኖር ነበር፡፡ ሁልጊዜም ማንም እንዳይሰማት በማድረግ ስትኖር ነብሩ የሚያማምሩትን ልጆቿን እያየ በመጎምዠት እርሷንም እንዴት ሊያታልላት እንደሚችል ያስብ ነበር፡፡
ታዲያ ከእለታት አንድ ቀን ነብሩ ከዋሻው አናት ላይ ካለ ዛፍ ላይ ተደብቆ ሳለ ኪናማ ከዋሻው ወጥታ ስትመለከት ማንንም ስላላየች በተለመደው ቆንጆ የድምጽ ቃና ጮክ ብላ “የኔ ዋሻ ሆይ! በርህን ዝጋ!” ካለችው በኋላ ፍየሎቿን ይዛ ሄደች፡፡
በዚህ ጊዜ ነብሩ ከዛፉ ላይ ዘሎ ወርዶ ወደ ዋሻው ሮጦ በመሄድ “ዋሻዬ ሆይ! በርህን ክፈት!” አለው፡፡
እናም ዋሻው ተከፈተ፡፡ ነብሩም ዋሻው ውስጥ ገብቶ ከአንድ የዋሻው ጉብታ ላይ ተደብቆ ተቀመጠ፡፡
ኪናማም ወደ ዋሻው ተመልሳ መጥታ “ግዙፉ ዋሻዬ ሆይ በርህን ክፈት!” ስትለው ዋሻውም ተከፍቶ ልጆቿን ሁሉ ይዛ ገብታ “ግዙፉ ዋሻዬ ሆይ! በርህን ዝጋ!” ስትለው መዝጊያው ተንሸራቶ ተዘጋ፡፡
ከዚያም ተቀምጣ እሳት ማቀጣጠል ስትጀምር ነብሩ ከላይ ካለ ጉብታ ላይ ሆኖ ለሃጩን ሲያዝረበርብ አንዲት ምራቅ ወርዳ እሳቱ ላይ ጠብ ስትል ኪናማ ነብሩ ዋሻው ውስጥ መሆኑን ወዲያው አወቀች፡፡ ጠረኑም ሸተታት፡፡
በዚህ ጊዜ “የጌታዬ ጠረን እየሸተተኝ ነውና እዚህ ዋሻ ውስጥ ነው ያለው፡፡” ብላ እሳቱን “እፍ! እፍ!” እያለች ማቀጣጠሏን ቀጠለች፡፡
አሁንም ሌላ የምራቅ ጠብታ ስትወድቅ ኪናማ “ጌታዬ እዚህ ዋሻ ውስጥ እንዳለ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ጠረኑንም በደንብ እያሸተትኩት ነው፡፡” አለች፡፡
ነብሩም ከተቀመጠበት ቦታ ሆኖ “አዎ! እዚህ ዋሻ ውስጥ ነኝ፡፡ አሁን የቱን ትመርጫለሽ ዘልዬ ወርጄ አንቺን ልግደልሽ ወይስ ዘልዬ ወርጄ ወፍራሙ ልጅሽን ዋርፖን ልብላው?” አላት፡፡
እርሷም “ታላቁ ጌታ ሆይ! ይህንን ወፍራሙን ዎርፖን ያሳደኩት ለአንተ እንደሆነ ታውቃለህ፡፡ እኔ ላይ ለምን ትዘላለህ? ዎርፖ ላይ ዘለህ ግደለው፡፡” አለችው፡፡
ነብሩም ዘሎ ወርዶ ዎርፖን በማነቅ ደሙን መጠጠው፡፡ ኪናማም “አሁን ጌታዬ ስጋውን ላዘጋጅልህ፡፡” አለችው፡፡ እርሱም “አዎ፣ አዘጋጂ፡፡” አላት፡፡
እርሷም ዋርፖን ከገፈፈች በኋላ “ስጋውን የምቀቅልበት ውሃ ያስፈልገኛል፡፡” ስትለው ነብሩም “ወደ ወንዙ ሄደሽ ይዘሽ ነይ፡፡” አላት፡፡
እርሷም ከዋሻው ወጥታ ውሃውን ቀድታ ተመለሰች፡፡ ታዲያ ውሃውን ከቀዳችበት ወንዝ ውስጥ አንድ ጬላ ግላካ የተባለ ትልቅ ነጭ ድንጋይ ይዛ ተመለሰች፡፡ ድንጋዩንም በዋርፖ ጮማ ስጋ ጠቅልላ ካዘጋጀች በኋላ ስቡን እሳቱ ላይ አድርጋ በጣም እንዲግል አደረገችው፡፡
ነብሩም በጣም ርቦት ስለነበረ ምራቁን ይውጥና ከንፈሮቹንም ይልስ ጀመር፡፡ እርሷም “ጌታዬ ሆይ! እኔ ላጉርስህ፡፡ አፍህን ክፈት፡፡”በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍሎች ሰውን ማጉረስ የአክብሮት መግለጫ ተደርጎ ይታሰብ ነበር፡፡ ስትለው “አአአ….” ብሎ አፉን በሰፊው ሲከፍት የጋለውን ድንጋይ አፉ ውስጥ ጨምራበት ገደለችው፡፡ አሁን ቀንደኛ ጠላቷን ስላስወገደችው በዚሁ ዓይነት ጅቡንም መግደል አሰበች፡፡ የልጇንም አጥንቶች አውጥታ በዋሻው በራፍ ላይ ስታስቀምጥ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ጅቡ መጥቶ “እነዚህ ሁሉ አጥንቶች ምንድናቸው?” አላት፡፡
እርሷም “ለአንተ ነው ያስቀመጥኳቸው፡፡ ለምን ወስደህ አትበላቸውም? ብዙ አጥንቶች አሉኝ፡፡ ብዙ ነገሮች አዘጋጅቼልሃለሁ፡፡” አለችው፡፡
እንደምታውቁት ጅብ ስግብግብ ነውና “አሃ! አዘጋጅተሽልኛል?” ሲላት “አዎ ብዙ የምትበላው ነገር አለኝ፡፡ ነገር ግን በአንድ ቅደመ ሁኔታ ብቻ ነው የምሰጥህ፡፡ ይኸውም የእኔንና ያንተን ጭራ አብሬ መስፋት ከቻልኩ ብቻ ነው፡፡” አለችው፡፡
ጅቡም ጓጉቶ ምራቁን እየዋጠ ነበርና “እሺ ስፊው፡፡” አላት፡፡ አጥንቶቹንም እየበላ እርሷ ቆዳውን እየወጋች ስትሰፋው “ተይ! ያማል!” ሲላት እርሷም “እንግዲያው አንተም መብላትህን ተው!” ትለዋለች፡፡
እርሱም “አይ ስለራበኝ መብላት እፈልጋለሁ፡፡” ሲላት “እንግዲያው መብላት ከፈለክ ጭራዎቻችንን መስፋት አለብኝ፡፡” ትለዋለች፡፡ ከዚያም “እሺ ቀጥይ” ይላታል፡፡
እርሷም የጅቡንና የነብሩን ጭራዎች በአንድ ላይ ሰፍታ ጅቡ አጥንቱን ቆረጣጥሞ ሲጨርስ “ጅብ ሆይ ጌታህ ነብር ቢመጣ ምን ታደርጋለህ?” አለችው፡፡
እርሱም “ተይ ባክሽ! ስሙን አትጥሪ፡፡ እርሱ ቢመጣ ህይወቴን ለማትረፍ ከዚህ እጠፋለሁ፡፡ በጣም ስለምፈራው በየቁጥቋጦው ላይና ባገኘሁት ነገር ላይ ዘልዬ ምናልባትም ገደል ውስጥ እገባለሁ፡፡” ሲላት እርሷም “እርግጠኛ ነህ?” ስትለው “አዎ” አላት፡፡
ከዚያም ጥቂት አጥንቶችን እስኪበላ ድረስ ጠብቃ “ጌታችን ኋላህ ነው! ነብሩ ኋላህ ነው!” አለችው፡፡
ጅቡም ዞር ብሎ ሲመለከት የነብሩን መልክ ያይና ሩጫውን ሲያስነካው የሁለቱ ጭራ በአንድነት ስለተሰፋ የነብሩን በድን አካል እየጎተተ በየቁጥቋጦው ላይ እየዘለለ ሄዶ ገደል ውስጥ ገብቶ ሞተ፡፡
ይህ የሚያሳየው ጭንቅላታችንን ተጠቅመን ጠላቶቻችንን ማሸነፍ እንደምንችል ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|