ክፉ መንፈስ ያለባት ሴት
በአይካበዳኔ ባሻ የተተረከ
በአንድ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ ክፉ ድርቅ ስለነበረ ሰዎች የሚበሉት ሲያጡ የዱር ፍሬዎችን እየለቀሙ ይበሉ ነበር፡፡ እናም ሁለት ልጆች የሚበሉትን ፍሬዎች ጫካ ውስጥ እየፈለጉ ሳለ አንደኛዋ ወደ አንደኛው የጫካ አቅጣጫ ስትሄድ ሁለተኛዋ ደግሞ ወደ ሌላ አቅጣጫ በመሄድ ፍሬዎችን መፈለግ ጀመሩ፡፡
ታዲያ በዚህ ጊዜ (ከጭንቅላቷ በኋላ በኩል ያሉትን ሁለት አይኖቿን በሻሽ የተሸፈነች) አንዲት ጭራቅ ሴት ወደ አንደኛዋ ልጅ መጥታ “ምን እያደረግሽ ነው?” ብላ ስትጠይቃት ልጅቷም “የምበላው ፍሬዎች እየፈለኩ ነው፡፡” አለቻት፡፡
“ስምሽ ማነው?”
“ስሜ ዱላ ይባላል፡፡ የምበላው ፍሬዎች እየፈለኩ ነው፡፡”
በዚህ ጊዜ ጭራቋ “እኔ ቤቴ ብዙ ለምግብነት የተዘጋጀ ጤፍጤፍ በኢትዮጵያ ደጋማ ሥፍራዎች የሚበቅል ሰብል ነው፡፡፣ ዳጉሳ፣ ስንዴና ገብስ ስላለኝ ፍራፍሬ ከምትለቅሚ ከእኔ ጋር እንሂድና ምግብ በልተሽ ወተት ትጠጫለሽ፡፡” አለቻት፡፡
ተያይዘውም ወደ ጭራቋ ቤት ሲደርሱ የጭራቋ ልጅ በቆሎ ትፈጭ ነበር፡፡
እናትየውም ወደ ጓዳው በሄደች ጊዜ የጭራቋ ልጅ እንግዳዋን ልጅ “እናቴ ምን ብላሽ ነው ይዛሽ የመጣችው?” ብላ ጠየቀቻት፡፡
ልጅቷም “እናትሽ እዚህ ብዙ ነገሮች እንዳሉ ነግራኝ ነው የመጣሁት፡፡” ስትላት የጭራቋ ልጅ “በይ አሁን ምንም እንዳትደነግጪ፤የምነግርሽንም ነገር ለእናቴ እንዳትነግሪያት፡፡ እናቴ ዋሽታሻለች፡፡ እዚህ ቤት ጤፍ፣ ስንዴም ሆነ ዳጉሳ የለም፡፡ የምንበላው የሰው ስጋ ነው፡፡ እዚህ ብዙ አጥንቶች አሉ፡፡ ከአይጦች ሰገራ ጋር አብሮ የተፈጨ አጥንት ነው የምንበላው፡፡ ወደ ጓዳ ወስዳሽ የተመረዘ ምግብ ትሰጥሻለች፡፡ ምግቡን ስትሰጥሽ እኛን አታየንምና ቀስ ብለሽ ለእኔ ስጪኝና እኔ እበላዋለሁ፡፡ መርዙ እኛን አይገድለንም፡፡” ካለቻት በኋላ ወደ መኝታቸው ሄዱ፡፡
ጭራቋ በሩ ላይ በክር የተንጠለጠለ ቃጭል አኑራለች፡፡ ስትተኛም እንቅልፍ እንደያዛት የሚያስታውቅባት ለየት ያለ የማንኮራፋት ድምፅ ታሰማለች፡፡ ታዲያ የጭራቋ ልጅ እንግዳዋን ልጅ “እናቴ ስትተኛ ማንኮራፋቷን ሰምቼ ስለማውቅ በሩን ቀስ ብዬ እከፍትልሽና ታመልጫለሽ፡፡” አለቻት፡፡
ልክ እንደተባባሉትም አድርገው ልጅቷ ወጥታ መሮጥ ጀመረች፡፡ ልጅቷ ሩጫዋን ያለማቋረጥ ተያያዘችው፡፡ ጭራቋም ከእንቅልፏ በነቃች ጊዜ በሩ መከፈቱን ስታይ “ወይኔ! ስጋዬ! አመለጠኝ፡፡ ወዴት እንደሄደች አይተሻል?” ብላ ልጇን ጠየቀቻት፡፡
ልጅቷም “አላየኋትም፣ተኝቼ ነበር፡፡” ስትላት “እንዴት ልታመልጠኝ ቻለች?” ብላ በጣም በብስጭት ነደደች፡፡ በዚህ ጊዜ ዱላ ወንዙን አቋርጣ ነበርና ጭራቋ ወንዙ ጋ ስትደርስ “ዱላ! ዱላ! ወንዙን እንዴት አቋረጥሽው?” ስትላት ዱላም “ወንዙ ላይ በተጋደመው ግንድ ላይ ሮጬ ነው የተሻገርኩትና አንቺም ይህንኑ አድርጊ፡፡” አለቻት፡፡
በዚህ ጊዜ አንድ አዞ ወንዙ ላይ ተጋድሞ ነበርና ጭራቋ በአዞው ላይ ሮጣ ልትሻገር ስትሞክር አዞው በላት፡፡
< ወደኋላ |
---|