ድመት፣አይጥና አውራ ዶሮ
በእማሆይ ዘውዲቱ ውድነህ የተተረከ
በአንድ ወቅት አንዲት የዋህ የአይጥ ግልገል እናቷን ሳታማክር ብቻዋን ውጪ፣ ውጪ ማለት ትጀምራለች፡፡
ከጉድጓድ ወጥታ ባየችው ነገር ሁሉ በመገረም ወደ አንድ በጣም ቆንጆ ነጭ ጥቅልል ብሎ የተኛ ድመት ዘንድ መጣች፡፡ ድመቱንም እንዳየችው በጣም ትወደዋለች፡፡
እንዲህም አለች “ይህ ፍጡር እንዴት ያምራል! ነጭ ፀጉሩና የሚያምሩ ጺሞቹ እጅግ ይማርካሉ፡፡ ሄጄም ላናግረው ይገባል፡፡ በጣም ስለሚያምር ልተዋወቀው እፈልጋለሁ፡፡”
ይህንን ብላ ወደ ድመቱ እየተሳበች ሳለ አንድ አውራ ዶሮ አየች፡፡ ዶሮው ግዙፍና አናቱ ላይ ቀይ ቆብ ያለው ሲሆን አይጧም በምንቃሩና በቆቡ ምክንያት ፈርታው ስለዘገነናት ወደ ኋላዋ አፈግፍጋ ወደ ድመቱ የምትደርስበትን አቋራጭ ስትፈልግ በድንገት ዶሮው ክንፎቹን አራግፎ አንድ ጊዜ ሲጮህ ደንግጣ በመሮጥ ወደ እናቷ ዘንድ ሄደች፡፡ እናቷም ልጇ ጠፍታባት ስለቆየች ተጨንቃ ነበር፡፡ እናም “በጣም ተጨንቄ ነበር፡፡ የት ሄደሽ ነው? ሳትነግሪኝስ ለምንድነው የወጣሽው?” አለቻት፡፡
ግልገሏም “እናቴ ሆይ! ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለምን ስላየኋት በጣም ተደስቻለሁ፡፡ ወፎችን አየሁ፡፡ ውሻንና ሌሎች የሚያማምሩ ነገሮችን አየሁ፡፡ ከዚያም የሆነውን ልንገርሽ፤ ወደ አንድ በጣም የሚያምር ፍጡርና ነጭ ፀጉርና ፂም ኖሮት ‘ሚያው’ እያለ በሚያወጣው ድምፁ ሁሉንም ወደሚስበው እንስሳ ሄጄ ጓደኛ ልሆነው ስሞክር አንድ አናቱ ላይ ቀይ ቆብ ያለው ግዙፍ ፍጡር አንድ ጊዜ ክንፎቹን አማቶ ቢጮህብኝ ሊበላኝ ነው ብዬ ስለፈራሁ ልነግርሽ እየሮጥኩ ወደቤት መጣሁ፡፡” አለቻት፡፡ እናትየውም “ትንሽና የዋህ በመሆንሽ ይህንን ሁሉ አለማወቅሽ እንዴት ያሳዝናል! ወዳጅና ጠላቷን የማትለይ ትንሽ ልጅ! ያ ፈርተሽ የሸሸሽው ፍጡር በጣም የዋህ ነው፡፡ ዝርያችንንም በምንም ዓይነት አያጠቃም፡፡ እንዲያውም ሰዎች አርደውት ሥጋውን ሲበሉ ለእኛ አጥንቶቹ ይተርፉናል፡፡ ነገር ግን በጣም ቆንጆና ሰላማዊ የመሰለሽ ፍጡር ድመት ሲሆን የምንደበቀውና የምንሸሸው የዝርያችን ጠላት ስለሆነ በፍፁም ሁለተኛ እንዳትጠጊው፡፡” ብላ መከረቻት፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|