ድሃው ሰውና እድሉ
በሺርጉማ ሶራጋ የተተረከ
በአንድ ወቅት በአንዲት መንደር ይኖር የነበረ አንድ ምስኪን ሰው በመንገዱ ላይ አንዲት በጣም ቆንጆ ሴት ታገኘውና “ወዴት እየሄድክ ነው? ምንስ ልታደርግ ነው?” ብላ ስትጠይቀው እርሱም “ስራ ሰርቼ ገንዘብ አግኝቼ ሃብታም መሆን እፈልጋለሁ፡፡” አላት፡፡
እርሷም “እኔ ሃብታም አደርግሃለሁ፡፡” አለችው፡፡
ከዚያም ወደ ቤቷ ወስዳው ከተራራ ላይ የሚዘራውን ዘር ሰጠችው፡፡ እርሱም ዘሩን ይዞ ወደ ማሳው ሲመለስ አንድ ሰው ማገዶ ሲሰበስብና ሲከምር ቢያየውም ሰውየው በፍፁም ደስተኛ አይመስልም ነበር፡፡
ማገዶውን በገመድ እያሰረ ከዚያም ሌላ ሊሰበስብ ይመላለስ ነበር፡፡ ከዚያም መሸከም የሚያቅተውን ያህል ማገዶ ከሰበሰበ በኋላ በአንድ ላይ በማሰር ሸክሙን በጀርባው ሊሸከም ቢሞክርም ያቅተዋል፡፡ እንደዚህም ሆኖ ሰውየው ተጨማሪ ማገዶ ለመልቀም መመላለሱን አላቆመም፡፡ አሁንም ሊሸከም ቢሞክርም ያቅተዋል፡፡ በዚህ ጊዜ መንገደኛው ሰው “ይህንን ሁሉ ማገዶ ከምረህ እንደማትችለው ስታውቅ ለምን የተወሰነውን ቀንሰህ የቻልከውን ያህል ብቻ አትሸከምም?” ሲለው ሰውየውም “ይህ አንተን አይመለከትህምና ዝም ብለህ መንገድህን ቀጥል፡፡” ብሎ መለሰለት፡፡
እርሱም ጉዞውን ቀጥሎ አንድ እህል የሚያጭድ ሰው ዘንድ ደረሰ፡፡ ይህ ሰው ታዲያ ሰብሉን በሙሉ የደረሰውንም ያልደረሰውንም ያጭድ ነበር፤ ጤፉንናበኢትዮጵያ ደጋማ ስፍራዎች የሚበቅል ሰብል ነው፡፡ ገብሱን ያልደረሰውንም አብሮ ያጭድ ነበር፡፡
መንገደኛውም ሰው “ለምንድነው እንደዚህ የምታደርገው? ያልደረሰውን ትተህ የደረሰውን ብቻ ለምን አታጭድም?” አለው፡፡
ይኸኛውም ሰው “አንተ ማነህና ነው ምን ማድረግ እንዳብኝ የምትነግረኝ፡፡ አርፈህ ጉዞህን ቀጥል፡፡” አለው፡፡
እርሱም መንገዱን ቀጥሎ ለሶስተኛ ጊዜ ያገኘው ሰው ትልቅ አለት እየገፋ ነበር፡፡
በዚህ ጊዜም ሰውየውን “ምን እያደረክ ነው?” አለው፡፡
“አለት እየገፋሁ ነው፡፡” ብሎ አሁንም ሙከራውን ቀጠለ፡፡ መንገደኛውም ሰው “ሆኖም አትችለውም እኮ! በጣም ትልቅ እኮ ነው!” ሲለው ሰውየው “መሞከሩ የእኔ ድርሻ ነው አንተን ምንም አያገባህምና የአለቱን ጉዳይ ለእኔ ተወውና አርፈህ መንገድህን ቀጥል፡፡” አለው፡፡
ከዚያም መንገደኛው ሰው ወደ ማሳው ሄዶ ዘሩን ዘርቶ ከጨረሰ በኋላ ወደ ቤቱ ሲመለስ ቆንጆዋ ሴት አግኝታው “በመንገድህ ላይ ምን አየህ?” ብላ ጠየቀችው፡፡
እርሱም ስለ ሶስቱ ሰዎችና ስላሉት ነገር ነገራት፡፡ ማገዶውን ይከምር ስለነበረው ሰው ሲነግራት እሷም “ያ ሰው ማለት ገንዘብ አበዳሪ ነው፡፡ ሁልጊዜም ተጨማሪ ገንዘብ ይፈልጋል፡፡ ሁለተኛው ሰው ደግሞ ሞት ነው፡፡ ወጣት፣ ሽማግሌውን፣ ደካማና ጠንካራውን ሃብታምና ደሃን ሳይለይ ይገድላል፡፡ አለቱን ይገፋ የነበረውን ሰው እንዳይገፋ ነግረኸው የነበረ ቢሆንም ያ ሰው ማለት ሃሳብ ማለት ነው፡፡ በሃሳብ ተውጦ እጅግ በጣም በማሰብ ብዙ የሚመኝና በራሱ ጉዳይ ጭነት ስር የሚኖር ነው፡፡ በፍፁም የማይረካ ሲሆን ይህ ሰው በጣም ሃብታም መሆን የሚፈልግ ሰው ነው፡፡” አለችው፡፡
በመጨረሻም ሴትየዋ “አንተ መዝራት ያለብህ የሃባብ የዘር ፍሬዎችን ሲሆን ሃብታምም ትሆናለህ፡፡” አለችው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|